የፀረ ሙስና ትግሉ ውጤታማ እንዲሆን ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ኮሚሽኑ ጥሪ አቀረበ

318

ባህር ዳር (ኢዜአ) ህዳር 27 ቀን 2015 በክልሉ የተጀመረው የፀረ ሙስና ትግል ውጤታማ እንዲሆን ሙሰኞችን በማጋለጥ ለህግ ለማቅረብ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ የአማራ ክልል የስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ጥሪ አቀረቡ።

''ሙስናን መታገል በተግባር'' በሚል መሪ ሃሳብ  የፀረ ሙስና ቀን ምክንያት በማድረግ በባህር ዳር ከተማ የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው።

ኮሚሽነሩ አቶ ሃብታሙ ሞገስ በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር፤  ሙስናን በቁርጠኝነት መከላከል ካልቻልን ሀገራችን እንዳትረጋጋ፣ ኢኮኖሚው እንዲቀጭጭና ህብረተሰቡ በመንግስት ላይ እምነት እንዲያጣ ያደርጋል ብለዋል።

መንግስት ድርጊቱን ለመከላከልና ለማስቆም የሙስና መከላከል ንቅናቄ መፈጠሩን ገልጸዋል።

የተጀመረው የፀረ ሙስና ትግል ውጤታማ እንዲሆን ሙሰኞችን በማጋለጥ ለህግ  ለማቅረብ  ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ኮሚሽነሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር የአደረጃጀት ዘርፍ  አማካሪ ዶክተር ጋሻው አወቀ በበኩላቸው ፤ሙስናና ሌብነትን ሁሉም ሊጠየፍ እንደሚገባ ተናግረዋል።

መላ ህብረተሰቡ ሙስናን፣ ብልሹ አሰራርንና ሌብነትን  አምርሮ ሊታገል እንደሚገባም አሳስበዋል።

በምክክሩ ላይ የአመራሮች፣ የሃይማኖት አባቶችና  ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች  እየተሳተፉ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም