ህብረብሔራዊ አንድነት ለልማትና ዕድገታችን ትልቅ አቅም ነው - ነዋሪዎች

156

ሀዋሳ (ኢዜአ) ህዳር 27/2015 ህብረብሔራዊ አንድነት ለሀገራዊ ልማትና ዕድገታችን ትልቅ አቅም በመሆኑ የሀገራችንን ብልጽግና ለማፋጠን በመተጋገዝ ልንሰራ ይገባል ሲሉ የሲዳማ ክልል ነዋሪዎች ተናገሩ ።

ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የሲዳማ ክልል ነዋሪዎች እንደተናገሩት የብሔር ብሔረሰቦች ቀን መከበሩ አንዱ የሌላውን ማንነት እንዲያውቅ ከማስቻሉም በላይ መከባበርና ወንድማማችነትን ለማጉላት ጠቀሜታው የጎላ ነው ፡፡

የሀዋሳ ከተማ ነዋሪ አቶ ቦጋለ ቦርሳሞ ኢትዮጵያ የበርካታ ማንነት፣ ባህል፣ ቋንቋ፣ መልክዓ ምድር ባለቤት ናት ብለዋል።

እነዚህን ብዝሃነትና ህብረብሔራዊ ማንነታችንን ተጠቅመን መስራት ከቻልን ደግሞ ለልማትና ዕድገታችን ትልቅ አቅም የሚሆን ነው ብለዋል ፡፡

በመሆኑም አብሮነታችንን በማጠናከር ተባብረን መሥራት ይጠበቅብናል ነው ያሉት፡፡

17ኛው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል በሀገር ዓቀፍ ደረጃ በሀዋሳ የሚከበር መሆኑ እጅግ እንዳስደሰታቸው ገልፀው ያለንን የሠላምና የአብሮነት እሴት ለወደፊቱም አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል ፡፡

የቦና ወረዳ ነዋሪ አቶ መንገሻ ቦኮ በበኩላቸው ህብረብሔራዊ አንድነት የዘመናዊነትና የሠለጠነ ማህበረሰብ መገለጫ መሆኑን ተናግረዋል ፡፡

ሀገራችንን ካደጉት ሀገራት ተርታ ለማሰለፍ አንዱ የሌላውን ማንነት አክብሮ መኖር፣ በአብሮነት መስራትና ኢትዮጵያን መውደድ ለአማራጭ የሚቀርብ ጉዳይ አይደለም ብለዋል፡፡

"ልዩነትን ከማስፋት የምናተርፈው ውድቀት መሆኑን ተምረንበታል" ያሉት አቶ መንገሻ፤ ላለችን አንድ አገር ሠላምን ማስፈንና ለጋራ ልማት በጋራ መቆም ይገባናል ብለዋል ፡፡

"መከባበርና መተባበር አብሮ ለመኖር ቁልፍ ሚና ያለው ነው" ያሉት ደግሞ የጤጢቻ ወረዳ ነዋሪው አቶ ዳዊት ጋሴ ናቸው ፡፡

በመሆኑም እርስ  በርሳችን ተከባብረንና ተዋደን በመስራት አገራችንን ከድህነት ማውጣት ይገባል ብለዋል።

እንደ ሀገር አሁን የተገኘውን የሠላም አማራጭ በመጠቀም አብሮነትን ማጎልበትና በጋራ መስራት ከሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚጠበቅ መሆኑንም ተናግረዋል ፡፡

የሲዳማ ህዝብ ከሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ጋር ተከባብሮና ተዋዶ የመኖር እሴት ያለው ህዝብ እንደመሆኑ ቀኑን ሲያከብርም በሙሉ ልቡ ለኢትዮጵያዊ አንድነቱ በመስራት ነው ብለዋል።

ይህንን እሴት ለማሳደግም እንደ ዜጋ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንደሚወጡም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም