በሐዋሳ 17ኛውን የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ያለፀጥታ ሥጋት ለማክበር በቂ ዝግጅት ተደርጓል

98

ሐዋሳ (ኢዜአ) ሕዳር 27 /2015 በሲዳማ ክልል አዘጋጅነት በሐዋሳ ከተማ የሚከበረው 17ኛው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ቀን ከእንግዳ አቀባበል ጀምሮ እስከ ፍፃሜው ድረስ በሰላም እንዲጠናቀቅ የሚያስችል በቂ ዝግጅት መደረጉን የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ አስታወቀ፡፡

የሲዳማ ክልል ሠላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አለማየሁ ጢሞቲዎስ እንደተናገሩት በበዓሉ ለመታደም ከሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚሰባሰቡ እንግዶች የሐዋሳ ቆይታቸው ደህንነት የተጠበቀ እንዲሆን ዝግጅት ሲደረግ ቆይቷል፡፡

የክልሉ የፀጥታ አካላት ከአገር መከላከያ ሠላዊት፣ ከፌዴራል ፖሊስና የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ጋር ተቀናጅተው እየሰሩ እንደሚገኙ ጠቅሰው፤ የፌዴራልና የክልሉ የፀጥታ ኮሚቴዎች ባደረጉት የጋራ ግምገማ ዝግጅቱ በቂ መሆኑን ማረጋገጣቸውን ገልፀዋል፡፡

በክልሉ የተሻለ ፀጥታና ሠላም እንዲሰፍን ከህዝቡ ጋር በቅንጅት መሰራቱ ውጤት ማስገኘቱን ገልጸው፤ እንግዶችን በኢትዮጵያዊ ወንድማማችነት ተቀብሎ ለማስተናገድ ነዋሪዎች ከወዲሁ ቅድመ ዝግጅት ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

የእንግዶቹ ቆይታ ያማረ እንዲሆን የከተማው ነዋሪው ዝግጅት ማድረጉን ገልጸዋል።

በአጋዥ የፀጥታ ኃይልነት ከተዋቀሩ የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል ወጣት እንግዳ ከፍያለው ሐዋሳ በአሁኑ ወቅት እጅግ ሠላማዊ መሆኗን ጠቅሶ፤ በየክፍለ ከተማችን ተደራጅተን ለበዓሉ ድምቀት የድርሻችንን ለመወጣት እየሰራን ነው ብሏል።

ኢትዮጵዊ የሆነ እንግዳ አቀባበል ለማድረግ መዘጋጀታቸውንም ገልጾ፤ ሐዋሳ የሠላምና የአብሮነት ከተማ መሆኗን ለማሳየት በቂ ዝግጅት ሲል ተናግሯል፡፡

ሌላው የአጋዥ የፀጥታ ኃይል አባል አገኘው ሌዳሞ በበኩላቸው ከፀጥታ አካላት ጋር ጥምረት ፈጥረው እየሰሩ መሆናቸውን ነው የጠቀሰው።

የእንግዶችን ደህንነት ለማስጠበቅ ከፀጥታ አካላት የአሰራር መመሪያና ማብራሪያ እንደተሰጣቸውም እንዲሁ።

ከዚህ በፊት በከተማዋ የሚከበሩ ህዝባዊና ሐይማኖታዊ በዓላት በሠላም ተካሂደው እንዲጠናቀቁ መስራታቸውን ጠቅሶ ከነገ በስትያ በሃዋሳ ለሚከበወው የብሄር ብሄረሰቦች ቀን የምሽት ጥበቃን ጨምሮ የተጠናከረ ሥራ ለመስራት መዘጋጀታቸውን ተናግሯል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም