ኢንተርፖል በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ሽብርተኝነትን በመዋጋት ረገድ ኢትዮጵያ እያደረገች ያለውን ጥረት ይደግፋል

145

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 27 ቀን 2015 ዓለም አቀፉ የፖሊስ ድርጅት /ኢንተርፖል/በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ሽብርተኝነትን በመዋጋት ረገድ ኢትዮጵያ እያደረገች ያለውን ጥረት እንደሚደግፍ አስታወቀ።

በዓለም አቀፉ የፖሊስ ድርጅት /ኢንተርፖል/ የፀረ ሽብር  ማዕከል የአፍሪካና  የአውሮፓ  ማዕከል ሃላፊ ዳንኤል ዳምጃኖቪክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ባለው በ24ኛው የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ሕብረት ጠቅላላ ስብሰባ በመካፈል ላይ ይገኛሉ።

ሃላፊው ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ድንበር ዘለል ሽብርተኞችን መከላከል የኢንተርፖል ዋነኛ ተልእኮው መሆኑን ገልጸዋል።

በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ስጋት የሆነውን ሽብርተኝነት በመዋጋት የኢትዮጵያን የላቀ ሚና አድንቀው ዓለም አቀፉ የፖሊስ ድርጅት ይደግፋል ብለዋል።

በዓለም195 አገራትን በአባልነት ያቀፈው ኢንተርፖል በየአህጉራቱ ከሚገኙ የፀረ ሽብር የቀጣና ማዕከላት መካከል አንዱ በኬኒያ ናይሮቢ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

በተለይም የሽብርተኝነት ስጋት ባለበት የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ከሚመለከታቸው የአገራቱ የጉምሩክ፣ ኢሜግሬሸን፣ የፖሊስና ሌሎችም ተቋማት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው በቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በአዲስ አበባ እየተካሄደ ያለው የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ሕብረት ስብሰባም በርካታ ባለድርሻ ተቋማት ጋር ለመምከር ዕድል የፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።

ላለፉት አምስት ዓመታት ከየአገራቱ የጉምሩክ፣ ኢሜግሬሽን፣ ከፖሊስና ሌሎች ተቋማት ጋር በመቀናጀት ሽብርተኞችን ለመከላከል በርካታ እርምጃዎችን ወስዷል ብለዋል።

በስብሰባው የቀጣናው አገራት የጸረ ሽብር ትግል ተሞክሯቸውን ያጋሩ መሆኑን ጠቅሰው የኢትዮጵያ ልምድ የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም ኢንተርፖል በፀረ ሽብር ግዳጅ አፈጻጸም ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎችም አገራት የሚያደርጉትን ጥረት እንዲሁም ተሞክሮ እንዲለዋወጡና አቅማቸውን እንዲያጎለብቱ የሚያደርገውን ድጋፍና ትብብር ያጠናክራል ብለዋል።

በጸረ ሽብር የትግል እንቅስቃሴ ኢንተርፖል ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው በቀጣይም አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ኢትዮጵያ በቀጣናው የሽብር ተጋላጭነት ስጋት ካለባቸው አገሮች መካከል መሆኗን ጠቅሰው የመከላከል ስራው በተጠናከረ መልኩ ሊቀጥል ይገባዋል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም