በደቡብ ክልል አዲሱን ስርዓተ ትምህርት ታሳቢ ያደረገ የመምህራን አቅም ግንባታና የግብዓት አቅርቦት እየተከናወነ ነው - ቢሮው

154

ሐዋሳ (ኢዜአ) ህዳር 26 ቀን 2015 አዲሱን ስርዓተ ትምህርት ለመተግበር የሚያስችል የመምህራን አቅም ግንባታና የግብአት አቅርቦት እየተከናወነ መሆኑን የደቡብ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታወቀ፡፡

የቢሮው ሃላፊ ዶክተር ዲላሞ ኦቶሬ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ባለፈው ዓመት በሙከራ ደረጃ የተጀመረው ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ያለው አዲሱ ስርዓተ ትምህርት ዘንድሮ ወደ ሙሉ ትግበራ መግባቱን ገልጸው፤ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

አዲሱን ስርዓተ ትምህርት ተግባራዊ የማድረግ ሂደት ሰፊ የመምህራን አቅም ግንባታን የሚጠይቅ መሆኑንም ዶክተር ዲላሞ ተናግረዋል፡፡

በዚህም በዘንድሮው ዓመት የክልሉ መንግስት በመደበው ከ123 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ከ80 ሺህ ለሚበልጡ መምህራን በአዲሱ ስርዓተ ትምህረት ላይ ያተኮረ የአጭር ጊዜ ስልጠና መሰጠቱን ገልጸዋል፡፡

ስልጠናው በስርዓተ ትምህርቱ አስፈላጊነት፣ በማስተማሪያ ዘዴው፣ በመምህራን ድርሻና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ያተኮረና መምህራንን ከአዲሱ ስርዓተ ትምህርት ጋር ያስተዋወቀ ነው ብለዋል፡፡

በክልሉ ባሉ ሶስት የትምህርት ኮሌጆች አዲሱ ስርዓተ ትምህርት ላይ ያተኮረ የዲግሪ ፕሮግራም መጀመሩን ተናግረዋል፡፡

በዚህም 1 ሺህ 400 የሚሆኑ መምህራን በዲላ፣ ሆሳዕናና አርባምንጭ ትምህርት ኮሌጆች ትምህርታቸው እየተከታተሉ ነው ሲሉ ገልጸው በስራ ላይ ያሉ መምህራንን በአጭርና በረዥም ጊዜ ስልጠና አቅማቸውን የማጎልበት ስራ እንደሚከናወንም ገልጸዋል፡፡

ከስርዓተ ትምህርት ለውጡ ጋር ተያይዞ ያለውን የመጽሐፍት እጥረት ችግር ለመፍታት የሚያስችሉ አማራጭ መፍትሄ እየተወሰደ እንደሆነ ገልጸው፤ የ7ኛ እና 8ኛ ክፍል መጽሐፍት በአገር ውስጥ ታትሞ ለዞኖች መሰራጨት መጀመሩን ገልጸዋል፡፡

የተማሪውንና የመምህሩን ማስተማሪያ ጨምሮ በ92 የትምህርት አይነት የታተሙ 1 ሚሊዮን 509 ሺህ 292 የመጽሃፍት ኮፒዎች መዘጋጀታቸውንና ቀድመው የታተሙ መጽሃፍትም በጋሞ፣ ወላይታ፣ ከምባታ፣ ሃዲያ፣ ስልጤና ጉራጌ ዞኖች መድረሳቸውን ተናግረዋል፡፡

በክልሉ በ31 ቋንቋዎች የአንደኛ ደረጃ ትምህርት የሚሰጥ ሲሆን ከዚህ ውስጥ ዘጠኙ እስከ ስምንተኛ ክፍል የሚሰጥባቸው በመሆኑ በመጽሃፍ ህትመቱ ተካተዋል ብለዋል፡፡

በጌዴኦ ዞን ዲላ ከተማ የዳማ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህርት ትግስት ሆርዶፋ በአዲሱ ስርዓተ ትምህርት ዙሪያ ያገኙት ስልጠና ለመማር ማስተማር ስራቸው እገዛ እንደሚኖረው ጠቁመዋል።

በጋሞ ዞን አርባምንጭ ከተማ የገሮ ሙሉ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ8ኛ ክፍል ተማሪ ጽዮን ፋሲካ አዲሱ ስርአተ ትምህርት ጋር በተያያዘ የመማሪያ መጽሐፍት በፍጥነት እንዲደርስ የሚመለከተው አካል መስራት እንዳለበት ጠቁማለች።

በበበጀት ዓመቱ በክልሉ ከ3 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ሲሆን ከ500 ሺህ የሚበልጡት ደግሞ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ተማሪዎች መሆናቸውን ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም