የኢትዮጵያን ዘላቂ ልማትና ብልጽግና ለማረጋገጥ የምሁራን ጠንካራ ተሳትፎና ሙያዊ አበርክቶ ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ

144

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 26/2015 የኢትዮጵያን ዘላቂ ልማትና ብልጽግና ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የምሁራን ጠንካራ ተሳትፎና ሙያዊ አበርክቶ ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ።

"ለኢትዮጵያ ልዕልና የምሁራን ሚና" በሚል መሪ ሃሳብ አገር አቀፍ የምሁራን የውይይት መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

በኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ እና በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በጋራ በተዘጋጀው የውይይት መድረክ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋን ጨምሮ በርካታ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን እንዲሁም የምርምር ተቋማት ተሳትፈዋል።

የኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ብርሃነ መስቀል ጠና፤ በመድረኩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት የኢትዮጵያን ልማትና ብልጽግና እውን ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ምሁራን የማይተካ ሚና አላቸው ብለዋል።

በመሆኑም ምሁራን ለአገር ልማትና እድገት ለአንድ ዓላማ በጋራ እሴቶች ላይ በማተኮር እንዲሰሩ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የምሁራን ጠንካራ ተሳትፎና ሙያዊ አበርክቶ ወሳኝ መሆኑም አስገንዝበዋል።

ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከመማር ማስተማሩ ጎን ለጎን በጥናትና ምርምር ሥራቸው አካባቢያዊ፣ አገራዊ እና ቀጣናዊ ችግሮችን ሊፈቱ ይገባልም ነው ያሉት።

የምሁራን የጥናትና ምርምር ሥራዎች የአገሪቷን ብሔራዊ ጥቅም ከግምት ያስገቡ መሆኑን ማረጋገጥ ይገባልም ብለዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካና የእስያ ጥናትና ምርምር ማዕከል ባልደረባ ዶክተር ሳሙኤል ተፈራ፤ የምሁራን ተሳትፎ ላይ ያሉ ችግሮችን የሚያስቃኝ ጽሁፍ አቅርበዋል።

ምሁራን በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ሀሳብ ለመሰንዘር በመገናኛ ብዙኃን ላይ እምነት አለመጣል አንዱ ችግር መሆኑንም በተደረገ የዳሰሳ ጥናት መለየቱን ጠቁመዋል።

ከምንም ነገር በላይ አገርን ማስቀደም እና ለዚህም የሚጠበቀውን ድርሻ መወጣት የምሁራን ቀዳሚ ኃላፊነት ሊሆን ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም