በዓለም ዋንጫው የጥሎ ማለፍ ዙር የሶስተኛ ቀን ውሎ ጃፓን ከክሮሺያ ብራዚል ከኮሪያ ሪፐብሊክ ሩብ ፍጻሜውን ለመቀላቀል ይጫወታሉ

234

አዲስ አበባ(ኢዜአ) ሕዳር 26 2015 በኳታር አስተናጋጅነት እየተካሄደ በሚገኘው 22ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ዛሬ ጃፓን ከክሮሺያ፤ ብራዚል ከኮሪያ ሪፐብሊክ ሩብ ፍጻሜ ለመግባት ይፋለማሉ።

እስከ አሁን አራት አገራት ወደ ሩብ ፍጻሜ ገብተዋል።ከምሽቱ 12 ሰአት በአል ጃኑብ ስታዲየም ጃፓን ከክሮሺያ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ጃፓን የሞት ምድብ የሚል ስያሜ በተሰጠው ምድብ አምስት በስድስት ነጥብ አንደኛ ደረጃን ይዛ ወደ ጥሎ ማለፉ ገብታለች።

የአውሮፓ እግር ኳስ ኃያላን የሆኑትን ጀርመን እና ስፔን በተመሳሳይ 2 ለ 1 አሸንፋለች። በኮስታሪካ ደግሞ 1 ለ 0 ተሸንፋለች።

በምድብ ስድስት የነበረችው ክሮሺያ በመጀመሪያ የምድብ ጨዋታ ከአፍሪካዊቷ አገር ሞሮኮ ያለ ምንም ግብ አቻ ተለያይታ በቀጣይ ጨዋታዋ ካናዳን 4 ለ 1 ረታለች።

ከቤልጂየም ያለ ምንም ግብ አቻ በመለያየት በአምስት ነጥብ ሞሮኮን ተከትላ ወደ ጥሎ ማለፉ መግባቷ ይታወቃል።

ጃፓን እና ክሮሺያ በዓለም ዋንጫ ሲገናኙ የአሁኑ ለሶስተኛ ጊዜ ነው።

እ.አ.አ በ1998 በፈረንሳይ አስተናጋጅነት በተካሄደው 16ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ በምድብ ስምንት ተገናኝተው ዳቮር ሱከር በ78ኛው ደቂቃ ባስቆጠራት ግብ ክሮሺያ ጃፓንን 1 ለ 0 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።

ሁለቱ አገራት እ.አ.አ በ2006 ጀርመን ባስተናገደችው 18ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ በምድብ ስድስት ተገናኝተው ያለ ምንም ግብ አቻ ተለያይተዋል።

ጃፓን እና ክሮሺያ ከዚህ ቀደም ሶስት ጊዜ እርስ በእርስ ተገናኝተው አንድ አንድ ጊዜ ሲሸናነፉ አንድ ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥተዋል።

በነዚህ ሶስት ጨዋታዎች ሁለቱ አገራት በተመሳሳይ አራት ግቦችን አስቆጥረዋል።

የ40 ዓመቱ ትውልደ ሞሮኮዋዊ አሜሪካዊ ኢስማይል ኤልፋት የሁለቱን ብሔራዊ ቡድኖች ጨዋታ በመሐል ዳኝነት ይመራሉ።

ከምሽቱ 4 ሰአት በዓለማችን የመጀመሪያው ተገጣጣሚና ተነቃቃይ ስታዲየም ስታዲየም 974 የአምስት ጊዜ የዓለም ዋንጫ አሸናፊዋ ብራዚል ከኮሪያ ሪፐብሊክ ጋር የምታደርገው ጨዋታ ተጠባቂ ነው።

ብራዚል በምድብ ሰባት ሰርቢያን 2 ለ 0 እንዲሁም ስዊዘርላንድን 1 ለ 0 አሸንፋለች።

በመጨረሻ የምድብ ጨዋታዋ በአፍሪካዊቷ አገር ካሜሮን 1 ለ 0 ተረታለች።

ውጤቶቹንም ተከትሎ ብራዚል በስድስት ነጥብ ምድቧን በመሪነት በማጠናቀቅ ወደ ጥሎ ማለፉ ገብታለች።

በአንጻሩ ኮሪያ ሪፐብሊክ ወደ ጥሎ ማለፉ የገባችበት መንገድ ልብ አንጣልጣይ የሚባል ነበር።

በምድብ ስምንት የነበረችው ኮሪያ ሪፐብሊክ በመጀመሪያ ጨዋታዋ ከኡራጓይ ጋር ያለ ምንም ግብ አቻ ስትወጣ በሁለተኛ ግጥሚያዋ በጋና 3 ለ 2 ተሸነፈች።

ወደ ጥሎ ማለፍ የመግባት ብቸኛ እድሏ የነበረው ኮሪያ ሪፐብሊክ ከመመራት ተነስታ ከምድቧ ቀድማ ያለፈችውን ፖርቹጋልን 2 ለ 1 በማሸነፍ በአራት ነጥብ ወደ ጥሎ ማለፉ መግባት ቻለች።

ኮሪያ ሪፐብሊክ ከኡራጓይ ጋር ተመሳሳይ አራት ነጥብ ቢኖራትም ብዙ ጎል ባገባ በሚለው የፊፋ ሕግ 16ቱን ተቀላቅላለች።

ብራዚል እና ኮሪያ ሪፐብሊክ በዓለም ዋንጫ ሲገናኙ የአሁኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

ከዚህ ቀደም ሰባት ጊዜ እርስ በእርስ ተገናኝተው ብራዚል ስድስቱን በማሸነፍ የበላይነቱን ይዛለች። ኮሪያ ሪፐብሊክ አንድ ጊዜ አሸንፋለች።

በሰባቱ ጨዋታዎች ብራዚል 16 ግቦችን ስታስቆጥር ኮሪያ ሪፐብሊክ አምስት ጎሎችን ማስቆጠር ችላለች።

የ40 ዓመቱ ፈረንሳዊ ክሌመንት ቱርፒን የሁለቱን አገራት ጨዋታ በመሐል ዳኝነት ይመራሉ።

የዛሬ ጨዋታ አሸናፊዎች አርብ ሕዳር 30 ቀን 2015 ዓ.ም በሩብ ፍጻሜው ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ትናንት እና ከትናንት በስቲያ በተደረጉ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ኔዘርላንድስ፣ አርጀንቲና ፈረንሳይ እና እንግሊዝ ሩብ ፍጻሜን መቀላቀላቸው ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም