17ኛውን የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ሰላማዊ ሆኖ እንዲከበር ዝግጅት ተደርጓል- የሲዳማ ክልል ሠላምና ፀጥታ ቢሮ

189

ሀዋሳ (ኢዜአ) ህዳር 26/2015 በሀዋሳ ከተማ 17ኛውን የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ያለምንም የጸጥታ ችግር ለማክበር በቂ ዝግጅት መደረጉን የሲዳማ ክልል ሠላምና ፀጥታ ቢሮ አስታወቀ ፡፡

በዓሉ ሠላማዊ ሆኖ እንዲከበር ሲደረግ የቆየው ዝግጅት መጠናቀቁን ተከትሎ የፀጥታ ኃይሎችና አጋዥ የማህበረሰብ የፀጥታ አካላት የተሳተፉበት ሰልፍ ተካሂዷል፡፡

የሲዳማ ክልል ሠላምናፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አለማየሁ ጢሞቲዎስ በዚህ ወቅት እንደተናገሩት በዓሉ ያለምንም የፀጥታ ሥጋት ፍፁም ሠላማዊ ሆኖ እንዲከበር በቂ ዝግጅት ተደርጓል።

ከሁሉም የኢትዮጵያ ጥግ የሚመጡ እንግዶች ወደ ከተማዋ መጥተው እስኪመለሱ እንቅስቃሴያቸው ደህንነት የተሞላበት እንዲሆን አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸው የክልሉ የፀጥታ አካላት ከሀገር መክላከያ ሠላዊት ፣ ከፌዴራል ፖሊስና ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ጋር ተቀናጅተው እየሰሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

የኦሮሚያና የሌሎች አጎራባች ክልል የፀጥታ አካላትም ከተለያዩ አካባቢዎች ክልሉን አቋርጠው ወደ ሀዋሳ የሚመጡ እንግዶችን ደህንነት በማስጠበቅ ረገድ ትልቅ እገዛ እያደረጉ ነው ብለዋል ፡፡

ለበዓሉ የሚመጡ እንግዶችን በኢትዮጵያዊ ወንድማማችነት መንፈስ ተቀብሎ ለማስተናገድ የሀዋሳ ከተማ ነዋሪዎች ከወዲሁ ቅድመ ዝግጅት ማድረጋቸውን ተናግረዋል ፡፡

በአጋዥ የፀጥታ ኃይልነት የተዋቀሩ የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል ወጣት እንግዳ ከፍያለው ሀዋሳ በአሁን ወቅት እጅግ ሠላማዊ መሆኗን ጠቅሶ ወጣቶች በየክፍለ ከተማችን ተደራጅተን የአካባቢያችንን ሠላም እየጠበቅን ነው ብሏል ፡፡

በየአካባቢው ባህላዊና ኢትዮጵዊ የሆነ እንግዳ አቀባበል ለለማድረግ መዘጋጀታቸውን የተናገረው ወጣቱ ሀዋሳ የሠላምና የአብሮነት ከተማ መሆኗን ለማሳየት በቂ ዝግጅት አድርገናል ነው ያለው ፡፡

በሰልፉ ላይ የፌዴራልና የሲዳማ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና የፀጥታ አካላት ተገኝተዋል ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም