ቤኔፊት-ካስኬፕ በተባለ ፕሮጀክት የማስፋት፣ የመደገፍና የዓቅም ግንባታ ሥራዎች እየተከናወነ ነው

46
አዲስ አበባ መስከረም 18/2011 በኢትዮጵያ ባሉ ክልሎች የመንግሥት የግብርና ዕድገት ፕሮግራም ለማስፈፀም ቤኔፊት-ካስኬፕ በተባለ ፕሮጀክት የማስፋት፣ የመደገፍና የአቅም ግንባታ ሥራዎች እየተከናወነ መሆኑን የግብርናና እንስሳት ሃብት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ በኢፌድሪ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴርና በኢትዮጵያ  የኔዘርላንድ ኤምባሲ መካከል እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር ጥር 17 ቀን 2017 በተፈረመው የመግባቢያ ሰነድ መሠረት ቤኔፊት ፕሮጀክት የተቋቋመበትን ሥራ እያከናወነ ይገኛል፡፡ ፕሮጀክቱን በባለቤትነት የሚያስፈፅመውና የሚቆጣጠረው የግብርናና እንስሳት ሃብት ሚኒስቴር ነው፡፡ በሚኒስቴሩ የግብርና ተመራማሪ ዶክተር አካሉ ተሾመ ለኢዜአ እንዳሉት ፕሮጀክቱ በአምስት የዩኒቨርስቲ የምርምር ተቋማት በሰብል፣ በአገዳ ፣ በጥራጥሬ ፣ በእንስሳት መኖ እንዲሁም በአትክልትና ፍራፍሬ ላይ እየሠራ ይገኛል፡፡ ፕሮጀክቱ በአዲስ አበባ ፣ሀዋሳ፣ ባህርዳር፣ መቀሌና በጅማ እየተተገበረ እንደሚገኝም ነው የገለጹት፡፡ ለአብነትም በሀዋሳ በብቅል ገብስ፣ በማዳበሪያና በአፈር ለምነት ላይ፣ በአማራ ደግሞ በድንችና በከብት መኖ ላይ ፕሮጀክቱ እየተተገበረ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡ የቤኔፊት- ካስኬፕ የአሠራር ፍልስፍናን ለመገመገም መስከረም 21 ቀን 2011 ዓ.ም. በሀዋሳ የመስክ ምልከታ ፕሮግራም ይካሄዳልም ነው ያሉት ዶክተር አካሉ፡፡ በመስክ ምልከታው ከግብርና ሚኒስቴር፣ የምርምር ኃላፊዎች፣ ከዩኒቨርስቲ ማህበረሰብና አርሶ አደሮች የተወጣጡ አካላትና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ይገኛሉ፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም