የጂንካ ግብርና ምርምር ማዕከል ምርታማነትን የሚያሳድጉ የሰብል ዝሪያዎችን እያላመደ ነው

268

ጂንካ (ኢዜአ) ህዳር 25/2015 ምርታማነትን የሚያሳድጉ የሰብል ዝሪያዎችን በጥናትና ምርምር በማግኘት የማላመድ ሥራ እያከናወነ መሆኑን የጂንካ ግብርና ምርምር ማዕከል አስታወቀ።

ማዕከሉ በደቡብ ኦሞ ዞን በበና ፀማይ ወረዳ በአርሶ አደር ማሳዎች በኩታ ገጠም እየለማ ያለው የማሽላ ሰብል ተጎብኝቷል።

የማሽላ ምርትን በእጥፍ ማሳደግ የሚችልና ”መልካም” በሚል የተሰየመ ምርጥ የማሽላ ዘር መሆኑም ተገልጿል።

በምርምር ማዕከሉ የሰብል ምርምር የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ አወቀ ታደሰ ለኢዜአ እንደገለፁት ”መልካም” የተሰኘው የማሽላ ዝሪያ ከዚህ ቀደም በአካባቢው ከሚለማው የማሽላ ዝሪያ በተሻለ የአካባቢውን አየር መላመድና በሽታን መቋቋም የሚችል ነው።

ከዚህ ቀደም በአካባቢው ከሚለማው የማሽላ ዝሪያ በሄክታር ከ 10 እስከ 27 ኩንታል ምርት እንደሚገኝ ጠቁመው “መልካም” የተሰኘው የማሽላ ዝሪያ በሄክታር ከ45 እስከ 54 ኩንታል ምርት መስጠት እንደሚችል ገልጸዋል።

የማሽላ ዝሪያውን በሌሎች አካባቢዎችም ለማስፋፋት እንዲያግዝ የአርሶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደሮች ውጤት ላይ የልምድ ልውውጥና የመስክ ምልከታ በበና ፀማይ ወረዳ ወይጦ ክላስተር ተካሂዷል።

በመስክ ምልከታው የደቡብ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ያሲን ጉኣ፣ የደቡብ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ማቲዮስ አንየው፣ የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ንጋቱ ዳንሳን ጨምሮ የሰብል ተመራማሪዎችና አርሶ አደሮች ተሳትፈዋል።