ኢትዮጵያን ጨምሮ ታዳጊ አገራት የዲጂታል ዘርፍን ለማሻሻል እያከናወኑ ያሉትን ስራ የበለጸጉ አገራት ሊደግፉት ይገባል- የአውሮፓ ህብረት የፓርላማ አባል

161

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 24/2015 ኢትዮጵያን ጨምሮ ታዳጊ አገራት የዲጂታል ዘርፍን ለማሻሻል እያከናወኑ ያሉትን ስራ የበለጸጉ አገራት ሊደግፉት እንደሚገባ የአውሮፓ ህብረት የፓርላማ አባል ሚያፔትራ ኩምፓላ ናትሪ ገለጹ።

17ተኛው ዓለም አቀፍ የኢንተርኔት ጉባኤ በኢትዮጵያ አዘጋጅነት በአዲስ አበባ ላለፉት አምስት ቀናት ሲካሄድ ቆይቶ ትላንት ማምሻውን ተጠናቋል።

በጉባኤው ለመሳተፍ ከአውሮፓ ህብረት ፓርላማ የመጡት ሚያፔትራ ኩምፓላ ዓለም ካለችበት ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር የኢንተርኔት ተደራሽነት በሀገራት እድገት ውስጥ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ተናግረዋል፡፡

በዚህም ሀገራት፣ ለቴክኖሎጂ፣አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ፣አይሲቲ እና ኢንተርኔት ትስስር ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተው በመስራት እድገት እያስመዘገቡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡  

በመሆኑም ይህ የዲጂታል ግንባታ በተለይ የወጣቶችን ህይወት በፈጠራ ስራና  በእውቅት ለመምራት ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው ብለዋል።

ከዚህ አኳያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን የዲጂታል ተደራሽነት ለማሻሻል ያደጉ አገራት በማደግ ላይ ላሉት ድጋፍ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ነው የተናገሩት፡፡

ከዚህ አኳያ የአውሮፓ ህብረት የበኩሉን ድጋፍ እያደረገ መሆኑን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ የቴሌኮም ዘርፏን ለግሉ ሴክተር ክፍት በማድረግ የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታን ለማስፋት እየሰራች ያለው ስራ የሚደነቅ መሆኑንም ተናግረዋል።

ይህም የኢትዮጵያ ዲጂታል ዘርፍ እድገትን በማፋጠን ረገድ ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም