ወጣቶች ለአገር ሰላምና አንድነት የሚችሉትን ሁሉ አስተዋጽኦ ማበርከት እንዳለባቸው ተገለጸ

110

ጅማ( ኢዜአ)  ህዳር 24 ቀን  2015  ወጣቶች ለአገር ሰላምና አንድነት የሚችሉትን ሁሉ አስተዋጽኦ ማበርከት እንዳለባቸው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል አምባሳደር ዶክተር የሺ መብራት ገለጹ።

የጅማ ዩኒቨርሲቲ ከሰላም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር 'በጎነት ለአብሮነት' በሚል መሪ ሀሳብ በበጎነት ዙሪያ ያሰለጠናቸውን ከ1 ሺህ 500 በላይ ወጣቶች አስመርቋል።

በዚሁ መርሀ ግብሩ ላይ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባልና የሰላም ጉዳዮች ንኡስ ኮሚቴ ሰብሳቢ አምባሳደር ዶክተር የሺ መብራት ''በጎነት በጊዜና በቦታ የማይወሰን ተግባር ነው'' ብለዋል፡፡

በጎነት ሌሎችን ለማገልገል የሀብት ብዛትና የእውቀት ደረጃ የማይወስነውና የሕሊና እርካታ የሚሰጥ መሆኑንም ተናግረዋል።

በተለይም የኢትዮጵያ ወጣቶች ሌሎችን ለማገልገል መትጋት እና የወገን ደራሽ ወገን መሆኑን በተግባር ማሳየት አለባቸው ብለዋል።

ወጣቶች የኢትዮጵያን ሰላምና አንድነት የሚያጸኑ ተግባራት በማከናወን የተሻለች አገር መገንባት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

አምባሳደሯ አክለውም ወጣቶቹ በዩኒቨርሲቲው ያገኙትን ስልጠና በተግባር ላይ በመዋል በጎ ተግብራቸውን እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።

በሰላም ሚኒስቴር 'የበጎነት ለአብሮነት' ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ገመቺስ ኢቺሳ በበኩላቸዉ የሰላም ሚኒስቴር ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር ከ34 ሺህ 500 በላይ ሰልጣኞችን በአምስት ዙር አሰልጥኗል።

ዛሬ በጅማ ዩኒቨርሲቲ የሰለጠኑትን ጨምሮ ሁሉም ተመራቂ ወጣቶች ለቀጣይ አስር ወራት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ተመድበዉ የበጎ ፍቃድ ስራቸውን የሚከውኑ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ስልጠናው ከበጎነት እና ከመረዳዳት እሴቶች ባሻገር የስራ ፈጠራ ክህሎት፣ እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ጠቀሜታዎችን ያከተተ በመሆኑ ሰልጣኞች በህይወታቸው ላይ የተሻለ ለውጥ እንዲያመጡ ያግዛቸዋል ብለዋል።

የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶክተር ጀማል አባፊጣ በበኩላቸው 'የበጎነት ለአብሮነት' ስልጣና ያጠናቀቁ ተመራቂዎች የአገሪቷ ሰላም አምባሳደሮች መሆን አለባቸው ብለዋል።

ተመራቂዎቹ በበጎ ፈቃደኝነት በሚያገለግሉበት የአገሪቷ አካባቢዎች ሁሉ ለሰላምና ለአንድነት መትጋት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

ሰልጣኝ ወጣቶች በዩኒቨርስቲው ውስጥ በነበራቸው ቆይታ በርካታ የበጎ ፍቃድ ተግባሮችን መሳተፋቸውን ገልጸዋል።

የበጎ ፍቃድ ስልጠናቸውን አጠናቀው የተመረቁ ሰልጣኞች በግቢው በነበራቸውን ቆይታ በርካታ ቁም ነገሮችን ያገኙበት አጋጣሚ በመሆኑ ደስተኞች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በበጎ ፈቃድ በሚያገለግሉበት አካባቢ ሁሉ ለኢትዮጵያ ሰላምና አንድነት የሚችሉትን በጎ ተግባር ለማበርከት መዘጋጀታቸውንም ገልጸዋል።

ጅማ ዩኒቨርሲቲ ለአምስት ተከታታይ ዙሮች ከ10 ሺህ 700 በላይ በጎ ፍቃደኛ ሰልጣኞችን ከሰላም ሚኒሰቴር ጋር በመተባበር ተቀብሎ ማሰልጠኑም ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም