ፍርድ ቤቱ በህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ጥፋተኛ ያላቸውን ግለሰቦች በጽኑ እስራትና በገንዘብ ቀጣ

121

ጎንደር (ኢዜአ) ህዳር 24/2015 የማእከላዊ ጎንደር ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ጥፋተኛ ያላቸውን ሶስት ግለሰቦች እያንዳንዳቸውን በ17 አመት ጽኑ እስራትና በገንዘብ መቅጣቱን አስታወቀ፡፡

የፍርድ ቤቱ የህዝብ ግንኙነትና የኮሙኒኬሽን ባለሙያ ወይዘሮ ማስተዋል ወርቁ  ለኢዜአ እንደገለጹት  ግለስቦቹ የተቀጡት በቀረበባቸው ክስ ጥፋተኛ መሆናቸው በማስረጃ በመረጋገጡ ነው።

የፍርድ ቅጣቱ የተላለፈባቸው ንጉሴ አዱኛ ቻላቸው፣ ደሌ አቸነፍ ጎበዜና አምባቸው ግርማ እንግዳው የተባሉ ግለሰቦች መሆናቸውን ገልፀዋል።

በምእራብ ጎንደር ዞን መተማ  ወረዳ  ሻሽጌ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት ግለስቦቹ 10 ግለስቦችን በመተማ በኩል ወደ ጎረቤት ሀገር ለማስወጣት በተሽከርካሪ በድብቅ ለማጓጓዝ ሲሞክሩ በጸጥታ ሃይሎች ክትትል በመያዛቸው መሆኑን ተናግረዋል።  

ግለሰቦቹ በማእከላዊ ጎንደር ዞን አለፋ ወረዳ ሚያዝያ 3 ቀን  2014 ዓ.ም ሌሎች ለጊዜው ካልተያዙና የጦር መሳሪያ ከታጠቁ ሶስት ግለሰቦች ጋር በመሆን በህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ተሰማርተው የተገኙ ለመሆናቸው በአቃቤ ህግ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎች  መረጋገጡን አስረድተዋል፡፡

ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ትናንት ባስቻለው ችሎት የግለሰቦቹ ጥፋተኝነት በቀረበ ማስረጃ በመረጋገጡ እያንዳንዳቸውን በ17 አመት ጽኑ እስራትና በ20ሺ ብር እንዲቀጡ ውሳኔ መሰጠቱን  አስታውቀዋል፡፡

ግለሰቦቹ የቤተሰብ አስተዳዳሪና ከዚህ ቀደም የወንጀል ድርጊት የሌለባቸው መሆኑን ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ በቅጣት ማቅለያነት እንደያዘላቸው ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም