በሲዳማ ክልል ዘንድሮ ከ283 ሺህ ቶን በላይ ቡና ለገበያ ለማቅረብ እየተሰራ ይገኛል

177

ሐዋሳ  (ኢዜአ) ህዳር 24 ቀን 2015 በሲዳማ ክልል ዘንድሮ ከ283 ሺህ ቶን በላይ ጥራቱን የጠበቀና የታጠበ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ እየተሰራ እንደሚገኝ ተገለጸ።

የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ እንዳሉት፤ በሲዳማ ክልል የቡና ማሳን በማስፋትና ምርታማነትን በማሳደግ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው።

በክልሉ ደጋና ወይናደጋ አካባቢዎች ቡና በስፋት እንደሚመረት ጠቅሰው፤ ምርቱ በጥራት ተዘጋጅቶ የተሻለ ገቢ እንዲያስገኝ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅትና አያያዝ ላይ አርሶ አደሩ ግንዛቤው እያደገ መምጣቱን ጠቁመዋል።

በአሁኑ ወቅት በክልሉ 160 ሺህ ሄክታር መሬት በቡና ተክል መሸፈኑን ጠቁመው፤ የተሻለ ምርት የሚሰጡ ዝርያዎችን በመትከል የአርሶ አደሩን ገቢ በማሳደግ ኑሮውን ለመለወጥ እየተከናወኑ ያሉት ተግባራት አበረታታች ናቸው ብለዋል።

በርዕሰ መሰተዳድሩ የተመራው ከፍተኛ የክልሉ አመራር በበንሳና ቡራ ወረዳዎች በቡና የለማ ማሳን ተዘዋውሮ የጎበኘ ሲሆን የቡና ልማቱ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ መመልከታቸውን አንስተዋል።

አርሶ አደሩ ያረጀና ምርታማነቱ የቀነሰ የቡና እግርን በመጎንደልና ነቅሎ በአዲስ በመተካት እያከናወነ ያለውን ተግባር አድንቀው፤ ምርታማነትን የሚጨምሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ሀላፊ አቶ መስፍን ቃሬ በበኩላቸው ዘንድሮ በክልሉ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኩንታል ቡና ይሰበሰባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸው፤ ከዚህም 283 ሺህ ቶን የታጠበ እሸት ቡናና 40 ሺህ ቶን ደረቅ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በክልሉ በንሳ ወረዳ በቡና ልማት የተሰማሩት አርሶ አደር እርቅባለው ጨባ በባለሙያዎች በሚሰጣቸው እገዛ ከአራት ሄክታር በላይ በሆነ ማሳ ያለሙት ቡና ዘንድሮ ጥሩ ምርት እንደሚሰጥ ያላቸውን ተስፋ ገልጸው፤ ምርታማነትን ለማሳደግ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ኮምፖስት በማዘጋጀት ተገቢውን እንክብካቤ ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል።

በዚህም ዘንድሮ ከ80 ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ማቀዳቸውን ጠቁመዋል።

ከሁለት ሄክታር በላይ የቡና ማሳ ያላቸው አርሶ አደሮች በቀጥታ ለውጪ ገበያ ለማቅረብ የተሰጣቸውን ዕድል ለመጠቀም ዘንድሮ ፈቃድ እንደሚያወጡም ገልጸዋል።

ባለፈው ዓመት በአገር አቀፍ ደረጃ አምስተኛ ቡና ላኪ የነበረው የዳዬ በንሳ ቡና ኤክስፖርት ድርጅት ስራ አስኪያጅና ባለቤት አቶ አሰፋ ዱካሞ እንዳሉት፤ በስራቸው 2 ሺህ 500 ቡና አምራች አርሶ አደሮችን በመያዝ ያመረቱትን ቡና አዘጋጅተው ለውጪ ገበያ እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል።

አርሶ አደሮቹ ከቡና ተከላ እስከ ለቀማ ያለውን ሂደት በተገቢው መንገድ እንዲያከናውኑ አስፈላጊውን ስልጠና እንደሚሰጣቸውና ክትትል እንደሚደረግ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም