በቆይታችን ኢትዮጵያ በፈጣን እድገት ላይ የምትገኝና እንግዳ ተቀባይ ሀገር መሆኗን ማወቅ ችለናል- የዓለም አቀፉ የኢንተርኔት ጉባኤ ተሳታፊዎች

128

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 24/2015   በቆይታችን ኢትዮጵያ በፈጣን እድገት ላይ የምትገኝና እንግዳ ተቀባይ ሀገር መሆኗን ማወቅ ችለናል ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የ17ተኛው ዓለም አቀፍ የኢንተርኔት ጉባኤ ተሳታፊዎች ገለጹ።

17ተኛው ዓለም አቀፍ የኢንተርኔት ጉባኤ ባለፉት 5 ቀናት በአዲስ አበባ ሲካሄድ ቆይቶ ትናንት ማምሻውን ተጠናቋል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የጉባኤው ተሳታፊዎች የኢትዮጵያ ቆይታቸው አስደሳች እንደነበር ተናግረዋል፡፡  

የኡጋንዳ የፓርላማ አባል ሳራ ኦፔንዲ፤ ኢትዮጵያዊያን እንግዳ ተቀባይ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ይህም ቤቴ ያለሁ ያህል እንዲሰማኝ አድርጎኛል ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅትም ኢትዮጵያ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችን በመገንባት በመሰረተ ልማት ዘርፍ ፈጣን እድገት እያስመዘገበች መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡

ይህም ኢትዮጵያ የአፍሪካ ማዕከል መሆኗን በተግባር የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡  

በጉባኤው ለመታደም ከአሜሪካ የመጡት ብራንዴ ጊዩርኪንክ  በበኩላቸው፣ ''ኢትዮጵያ በጣም የወደድኳት ሀገር ነች '' ሲሉ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ለዓይን የሚማርኩ ባህላዊ አልባሳት፣ ጣፋጭ ባህላዊ ምግቦች እና እንግዳ ተቀባይ ሀገር መሆኗን በማንሳት ለኢትዮጵያዊያን ሰላምና ብልጽግና ተመኝተዋል፡፡

ከፊሊፒንስ የመጡት ሌላኛው የጉባኤው ተሳታፊ ሬድ ታኒ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ለመጀመሪያው ጊዜ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህም ኢትዮጵያ እጅግ ውብ ሀገር መሆኗን መገንዘብ ችያለሁ ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያዊያን እንግዳ ተቀባይ ህዝቦች መሆናቸውንም ነው የተናገሩት፡፡

ወደ መጡበት ሀገር ሲመለሱ ኢትዮጵያ ለእረፍት ምቹ ሀገር መሆኗን ለጓደኞቻቸው እንደሚናገሩም ነው የገለጹት፡፡

ከቻድ የመጡት ኩዚፊሳ ከዲድማን፤ ኢትዮጵያ ከሀገራቸው ጋር ተቀራራቢ ባህል ያላት መሆኗን ይናገራሉ፡፡

ለኢትዮጵያ ሙዚቃ፣ አልባሳትና ቡና አዲስ አለመሆናቸውን የተናገሩት ኩዚፊሳ ኪድድማን፤ ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያ ቆይታቸው እጅግ አስደሳች እንደነበር ገልጸዋል።

17ኛው የበይነ መረብ አስተዳደር ጉባኤ ከ170 በላይ የዓለም አገራት የመጡ ከ5 ሺህ በላይ ግለሰቦች በአካልና በበይነ መረብ መሳተፋቸውን ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም