ዓለም አቀፉ የበይነ መረብ አስተዳደር ጉባኤ ኢትዮጵያ ያላትን የዲጂታል አቅም ለዓለም እንድታስተዋውቅ እድል የፈጠረ ነው

140

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 24/2015 ዓለም አቀፉ የበይነ መረብ አስተዳደር ጉባኤ ኢትዮጵያ ያላትን የዲጂታል አቅም ለዓለም እንድታስተዋውቅ እድል የፈጠረ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ገለጸ።

በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት ከህዳር 19 እስከ 23 /2015 ሲካሄድ የነበረው 17ኛው የአለም የበየነ መረብ አስተዳደር ጉባኤ ትናንት ተጠናቋል።

በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጀነራል ዳሬክተር ዶክተር አብዮት ባዩ ለኢዜአ እንዳሉት ጉባኤው ለበይነ መረብ አስተዳደር ጠቃሚ ውይይቶችን በማድረግ በተሳካ ሁኔታ ተካሂዷል።

ጉባኤው በእቅዱ መሰረት እንግዶችን በመቀበል፣ የተለያዩ ጥናታዊ ጹህፎችና የፖሊሲ ውይይቶች የተከናወኑበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ታላላቅ ዓለም አቀፍ ምሁራንና ተጽእኖ ፈጣሪ ግለሰቦችን ጨምሮ በርካታ ሰዎችን ያሳተፈና ስኬታማ ጉባኤ እንደነበርም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ እየገነባች ላለው የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ  ልምዶችን የቀሰመችበትና ያላትንም ልምድ ለሌሎች ያካፈለችበት እንደነበርም እንዲሁ።

በዚህም በኢንተርኔት ተደራሽነት፣ መሰረተ ልማት በመገንባትና በሌሎች በዘርፉ የተሻለ ደረጃ ከደረሱ አገሮች ልምዶችን መውሰዷን ነው የገለጹት።

ያላትን የዲጂታል አቅም በዓለም አቀፍ ደረጃ በማስተዋወቅ በርካታ የኦንላይን ስራዎችን ወደ አገሪቱ ለማምጣት የሰራችበት እንደነበርም ገልጸዋል።

በተመሳሳይ በዓለም አቀፍ ደረጃ በቴክኖሎጂ ገበያ ላይ ውሳኔ የሚያሳልፉ፣ የዓለምን የቴክኖሎጂ ፖሊሲ የሚቀይሱ ተጽእኖ ፈጣሪ ሰዎች ኢትዮጵያ መጥተው መልካም ገጽታ ማየታቸው ለቀጣይ ስራ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ጨምረዋል።

በአዲስ አበባ በተካሄደው 17ኛው የበይነ መረብ አስተዳደር ጉባኤ ከ170 በላይ የዓለም አገራት የመጡ  በአጠቃላይ ከ5 ሺህ በላይ ግለሰቦች በአካልና በበይነ መረብ መሳተፋቸውን ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም