ፍርድ ቤቱ በአቶ አብዲ መሐመድ ኡመር እና ሌሎች ሶስት ተጠርጣሪዎች ጉዳይ ተጨማሪ የ10 ቀን የምርመራ ቀን ፈቀደ

66
አዲስ አበባ መስከረም 18/2011 ፍርድ ቤቱ በቀድሞ የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ አብዲ መሐመድ ኡመር እና ሌሎች ተጠርጣሪዎች ጉዳይ ተጨማሪ የ10 የምርመራ ቀን ፈቀደ። በሶማሌ ክልል በነበረው ሁከትና ብጥብጥ ላይ የሰብዓዊ  መብት ጥሰት በመፈጸምና ሄጎ የተባለ ህገ ወጥ ቡድን በማደራጀትና በማስተባበር  የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲፈጸም  ትዕዛዘ ሰጥተዋል በሚል ተጠርጥረው  ነው ለህግ የቀረቡት። በተጨማሪም  በሴቶች ላይ የአስገድዶ መድፈር ወንጀል እንዲፈጸም በዘርና በአኃይማኖት እንዲሁም በብሔር መካከል ግጭት በማስነሳት ወንጀል ተጠርጥረው  በህግ ቁጥጥር ስር ውለዋል። በዛሬው እለትም በፌደራል ከፍተኛ  ፍርድ ቤት ተረኛ  የወንጀል ችሎት ቀርበው  ጉዳያቸው ታይቷል። በዚህም  አንደኛ ተጠርጣሪ አቶ አብዲ መሐመድ ኡመር፣ 2ኛ ተጠርጣሪ ወይዘሮ ረህማ አህመድ፣ 3ኛ ተጠርጣሪ አብዱረዛቅ ሳኒ  እንዲሁም 4ኛ ተጠርጣሪ ፈርሃን ጣሂር  ሲሆኑ መርማሪ ፓሊሱ በክልሉ  በነበረው  ሁከትና ብጥብጥ  እነዚህ  ተጠርጣሪዎች ሄጎ የሚል ህገ ወጥ ቡድን  በማደራጀትና በማስታጠቅ በዜጎች ላይ የጂምላ  ጨፍጨፋ ፈጽመዋል በማለት ለፍርድ ቤተ አስረድተዋል። በዚህም መርማሪ ፖሊስ ተጠርጣሪዎች ከተያዙበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ የምርመራ ስራዎች እየሰራ የሰውና የሰነድ ማስረጃ ሲያደራጅ መቆየቱን ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል። ይሁን እንጂ በክልሉ የተፈጸሙ ወንጀሎች ውስብስብና ከባድ እንዲሁም የሰው ህይወት ያለፈበት በመሆኑ ከተፈጸመው ወንጀል አንጻር ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንደሚያስፈልገው አስረድተዋል። በመሆኑም ተጨማሪ የሰውና የሰነድ ማስረጃ ለማሰባሰብ ፍርድ ቤቱን ተጨማሪ የ15 ቀን እንዲፈቀድለት ጠይቀዋል። ተጠርጣሪዎች በበኩላቸው የተጠየቀው ጊዜ ተገቢነት የለውም ፣ ከዚህም በፊት ሲነሱ የነበሩ ጥያቄዎችን መልሰው በማንሳት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ መጠየቃቸው አግባብነት የለውም ብለዋል። እንዲሁም በእስር ቤቱ ያለው አያያዝ ችግር እንዳለበት ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል። ሁሉም ተጠርጣሪዎች የጤና እክል ያለባቸው በመሆኑ ፍርድ ቤቱ ይፈቀደልን የህክምና አገልግሎት እንዳናገኝ ተደርገናል ሲሉም አክለዋል። የግራና ቀኙን ክርክር ያዳመጠው የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የተረኛ ወንጀል ችሎት የተጠርጣሪዎችን አያያዝ በተመለከተ ህክምናው እንዲስተካከልና በተገቢው መልኩ እንዲከታተሉት ትዕዛዝ ሰጥቷል። መርማሪ ፓሊስ የጠየቀውን የ15 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ውድቅ በማድረግም ተጨማሪ የ10 ቀን የምርመራ ጊዜ ፈቅዷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም