የፀረ-ሙስና ንቅናቄው ውጤታማ እንዲሆን የህዝቡ ድጋፍ ወሳኝ ነው–የአማራ ክልል ስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን

597

ባህር ዳር (ኢዜአ) ህዳር 23/2015 በአማራ ክልል የፀረ-ሙስና ንቅናቄ ትግሉ ውጤታማ እንዲሆን ህዝቡ አስፈላጊውን ጥቆማና ድጋፍ በማድረግ በቁርጠኝነት ድጋፍ ሊያደርግ ይገባል ሲሉ የአማራ ክልል ስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ሃብታሙ ሞገስ አስገነዘቡ።

የክልሉ ስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ዓለም አቀፍ የፀረ-ሙስና ቀንን ምክንያት በማድረግ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።

ኮሚሽነር ሃብታሙ በሰጡት መግለጫ ባለፉት ሁለት ዓመታት የፀረ ሙስና ትግሉ ተቀዛቅዞ መቆየቱን አመልክተዋል።

ሙስና አሁን ላይ ህዝቡን ክፉኛ ያስመረረና አስቸጋሪ ደረጃ ላይ መድረሱን ጠቅሰው፤ ሙስናን ለመከላከልና ለማስቆም በአዲስ ንቅናቄ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በአገር ደረጃ የተጀመረው የፀረ-ሙስና ትግል ንቅናቄ በክልል ደረጃም ውጤታማ እንዲሆን ህዝቡ አስፈላጊውን ጥቆማና በፍርድ ቤትም ምስክር በመሆን ሊያግዝ ይገባል ብለዋል።

የፀረ ሙስና ትግሉ በከፍተኛ አመራሩ አጀንዳ ሆኖ መሰራት መጀመሩን አመልክተው፤ በኮሚሽን ደረጃም ትግሉን ለማቀጣጠል ከፖሊስና አቃቢ ህግ ተቋም ጋር በመሆን በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ኮሚሽነር ሃብታሙ አክለውም ያለ ህብረተሰቡ የነቃ ተሳትፎ የፀረ-ሙስና ንቅናቄው ውጤታማ እንደማይሆን ጠቅሰው፤  ህብረተሰቡ ሙስናን ለማስወገድ በባለቤትነት መንፈስ መሳተፍ ይጠበቅበታል ብለዋል።

በተለይም የሃይማኖት አባቶች ህዝቡን በማስተማር፣ የዴሞክራሲ ተቋማት፣ ሲቪክ ማህበራትና መገናኛ ብዙሃን ሙስናን ለመከላከል የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት መወጣት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

የፀረ ሙስና ቀን ሲከበርም አሁን የተጀመረውን ንቅናቄ ወደ ህብረተሰቡ በትክክል ማውረድ በሚያስችል አግባብ መሆን እንዳለበትም አመላክተዋል።

በሃገር አቀፍ ደረጃ ለ18ኛ ጊዜ የሚከበረው የፀረ-ሙስና ቀን በአማራ ክልል ደረጃ ህዳር 27 ቀን 2015 ዓ.ም በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሮ እንደሚውል ከወጣው መርሃ ግብር ማወቅ ተችሏል።