በሐረሪ ክልል የመሰረተ ልማት አውታሮችን በፍትሃዊነት ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው - የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ

148

ሐረር (ኢዜአ) ህዳር 23 ቀን 2015በሐረሪ ክልል በገጠርና በከተሞች የመሰረተ ልማት አውታሮችን በፍትሃዊነት ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ አስታወቁ።

በክልሉ ኤረር ወረዳ በ83 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር ወጪ የተገነቡ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ተመርቀው ለአገልግሎት ብቁ ሆነዋል፡፡

ከፕሮጀክቶቹ መካከል ትምህርት ቤትና የአምስት ኪሎ ሜትር የጠጠር መንገድ ይገኙበታል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በፕሮጀክቶቹ የምረቃ ስነ-ስርዓት ላይ እንዳሉት በገጠሩ አካባቢ የሚስተዋለውን የትምህርት መጠነ ማቋረጥ ችግር ለማቃለልና የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ጥረት እየተደረገ ነው።

በክልሉ በቀጣይ አስር ዓመታት ሶስት ተጨማሪ ከተሞችን ለመመስረት ከታቀዱት ውስጥ አንዱ በኤረር ወረዳ አካባቢ መሆንና ለዚህም አስፈላጊውን መሰረተ ልማት የማሟላት ስራ እየተከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

በወረዳው የተገነባው የጠጠር መንገድ ፕሮጀክትም አርሶ አደሩ ምርቱን ለገበያ እንዲያቀርብ ምቹ ሁኔታ ከመፍጠሩም ባሻገር የጤና ፣ የትምህርትና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን ተደራሽ ለማድረግ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው አስረድተዋል።

በክልሉ በገጠርና በከተሞች ፍትሃዊ የመሰረተ ልማት አቅርቦት እንዲኖር የክልሉ መንግስት በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የክልሉ መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ ኢንጅነር ጠይባ አብደላ በበኩላቸው፤ የክልሉ መንግሥት ከዋና መስመሮች፣ ከአጎራባች ወረዳዎችና ከተሞች ጋር የሚያገናኙ መንገዶችን ለመገንባት እየሰራ ነው ብለዋል፡፡

በኤረር ወረዳ የነበረውን የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት ችግር ለመፍታት ለምረቃ የበቃው አዲስ ትምህርት ቤት መገንባቱን የገለጹት ደግሞ  የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙክታር ሳሊህ ናቸው።

ምቹ የመማር ማስተማር ሂደትን ለማቀላጠፍ ቀድሞ በነበረው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የማስፋፊያ ግንባታ መከናወኑን አስታውቀዋል።

የኤረር ወረዳ ነዋሪ አቶ አብዱሰላም ደሲ በሰጡት አስተያየት፤ ካሁን ቀደም በወረዳው የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት ባለመገንባቱ ልጆቻቸው ትምህርት ሳያገኙ ይቀሩ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

አሁን ላይ በወረዳው የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት መገንባቱ ልጆቹም ትምህርት እንዲያገኙ እድል በመፍጠሩ መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡

የኤረር ወልዲያ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር ዘውዱ ግርማ፤ ካሁን ቀደም በወረዳው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ቢኖርም ካለው የተማሪ ቁጥር ጋር የሚጣጣም እንዳልነበረ ተናግረዋል፡፡

አሁን ላይ ለትምርት ቤቱ  የማስፋፊያ ግንባታ ተደርጎለት አስፈላጊው ግብአት በመሟላቱ ችግሩ መቃለሉን ገልጸዋል፡፡  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም