አገር አቀፍ የምሁራን የምክክር መድረክ በመጪው ሰኞ በአዲስ አበባ ይካሄዳል

171

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 23/2015 አገር አቀፍ የምሁራን የምክክር መድረክ በመጪው ሰኞ በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ተገለጸ፡፡

የምክክር መድረኩን ያዘጋጁት የኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ እና የአዲስ  አበባ ሳይንስና ቴክሎጂ ዩኒቨርሲቲ በጋራ  በመሆን ነው፡፡

የኮተቤ  ትምህርት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ብርሃነመስቀል ጠና እና የአዲስ አበባ  ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ደረጀ  እንግዳ መድረኩን አስመልክተው በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

የኮተቤ  ትምህርት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ብርሃነመስቀል ጠና በዚሁ ጊዜ በመድረኩ ከተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች፣ምርምር ተቋማት እና ባለድርሻ ተቋማት የተውጣጡ ከ300 በላይ ግለሰቦች እንደሚሳተፉ ተናግረዋል፡፡

መድረኩ በዋናነት  ምሁራን በአገር ልማት ላይ የሚጠበቅባቸውን በጎ ሚና እንዲወጡ በሚያደርጉ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደርጋል ነው ያሉት፡፡

በዚህም  በመልካም  አስተዳደር እንዲሁም በኢኮኖሚ  እድገት ላይ ኢትዮጵያን የሚያሻግሩ ሀሳቦች እንደሚነሱ ይጠበቃል ብለዋል፡፡

መድረኩን ለማዘጋጀት  ለሁለት ወራት  ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱን ጠቅሰው፤  ለውይይት መነሻ የሚሆኑ ጹሁፎች እንደሚቀርቡም ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ  ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ደረጀ  እንግዳ በበኩላቸው መድረኩ በተለይ በዘላቂ ሰላም ግንባታ ላይ ምሁራን ሚናቸውን እንዲወጡ እድል የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም