ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም ኃላፊ ጋር ተወያዩ

103


አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 23/2015 ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም ኃላፊ አቺም ስቴነር ጋር ተወያዩ።

በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ በሚመለከት ገለፃ ያደረጉት አቶ ደመቀ መንግስት የሰላም ስምምነቱ ተፈፃሚ እንዲሆን የያዘውን ቁርጠኛ አቋምም ለሃላፊው ገልጸዋል።

በአሁን ሰዓት መንግስት በዋናነት የመልሶ ግንባታ፣ ሰብዓዊ ድጋፍ ማቅረብና ተጠያቂነት ማስፈን በሚሉ ሦስት ዋና የትኩረት አቅጣጫዎችን መሰረት በማድረግ ወደ ስራ መግባቱን አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት አመታት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ስታልፍ እና ያልተገባ ጫና ሲደርስባት የልማት ድርጅቱ ለኢትዮጵያ ላሳየው አጋርነት አመስግነዋል።

በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባት እና ህብረተሰቡን ለመደገፍ ልዩ ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ ስራ በመግባት ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች ያልተቋረጠ የሰብዓዊ አቅርቦት በተለያዩ አቅጣጫዎች ተደራሽ እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በአንዳንድ አካባቢዎች የትምህርት፣ ኤሌክትሪክ፣ ቴሌኮሙኒኬሽን እና ሌሎች አገልግሎቶች ዳግም መጀመራቸውን ጠቅሰዋል።

የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም የመልሶ ማቋቋም ስራን በማገዝ ከመንግስት ጎን መቆም እንዳለበት ነው ያስታወቁት።

የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም ኃላፊ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የነበረውን ችግር በሰላም ስምምነት ለመቋጨት መንግስት ያሳየውን ቁርጠኝነት አድንቀዋል።

በጦርነት የወደሙ አካባቢዎችን መልሶ ለማቋቋም ድርጅታቸው አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍና ትብብር እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

ሌሎችም አጋር አካላት በመልሶ ግንባታ ሂደት ላይ ትብብር እንዲያደርጉ በድርጅታቸው በኩል ስራዎች እንደሚሰሩም ቃል መግባታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት መረጃ ይጠቁማል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም