የሌማት ትሩፋት መርሀ-ግብር የሴቶችን ጫና በመቀነስ ረገድ ጉልህ ሚና አለው-ከንቲባ አዳነች አቤቤ

150

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 23/2015 የሌማት ትሩፋት መርሀ-ግብር የሴቶችን በተለይም የእናቶችን ጫና በመቀነስ ረገድ ጉልህ ሚና እንዳለው የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ።

የብልጽግና ፓርቲ የሴቶች ሊግ በከተማዋ የተጀመረውን የሌማት ትሩፋት  ማስቀጠያ መርሀ-ግብር በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ አካሂዷል።

የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የሌማት ትሩፋት በተደራጀ ተሳትፎ ከታገዘ በሴቶች ሕይወት ላይ ለውጥ ለማምጣት ትልቅ አጋጣሚ ነው።

እናቶች ባላቸው ተሰሚነት ልጆቻቸውን በማሳመን በሌማት ትሩፋቱ በንቃት ተሳትፎ እንዲያደርጉ ከንቲባ አዳነች ጥሪ አቅርበዋል።

የከተማው ሴቶችን በኢኮኖሚው መስክም በመተባበርና በእልህ የምንሰራበት ጊዜ አሁን ነው ብለዋል።

የብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ ምክትል ፕሬዝዳንት ወይዘሮ ጠይባ ሐሰን በበኩላቸው የሌማት ትሩፋት ዕቅድ የመዲናዋን ሴቶች የሚያሳትፍና ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ መሆኑን አመልክተዋል።

ወይዘሮ ጠይባ አያይዘውም የሌማት ትሩፋት አገርን የሚገነባ ንቁና ዕውቀት ያለው ትውልድ ለማፍራት በምግብ ራስን ለመቻል ወሳኝ መርሀ ግብር መሆኑን አስገንዝበዋል።

'በአረንጓዴ አሻራና ምግቤን ከጓሮዬ' መርሀ-ግብር የተሰራው ሥራ የሚደነቅ መሆኑን ጠቁመዋል።

በመርሀ ግብሩ ላይ ለዘማች ቤተሰቦች፣ ለአካል ጉዳተኞችና ብቻቸውን ልጆች እያሳደጉ ላሉ እናቶች የጓሮ እርሻና ዶሮ በማርባት ዕንቁላል የሚያመርቱበት ቦታ በስጦታ ተበርክቶላቸዋል።

በሌማት ትሩፋቱ ስጦታ የተበረከተላቸው እናቶች ኑሮአቸውን የሚደጉሙበትና ልጆቻቸውን የሚያሳድጉበት ተጨማሪ ገቢ በማግኘታቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።

የተሻለ ገቢ ለማምጣትም ጉልበትና ቦታ የማይፈጁ የጓሮ አትክልት ሥራዎችን በመሥራት የኑሮ ውድነቱን ለማሸነፍ እንሰራለን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም