ህዝቡ በሃገሩ ላይ የተቃጣውን ጥቃት በመመከት ለህዳሴው ግድብ በሚያደርገው ድጋፍ መከታነቱን አሳይቷል…አቶ አወሉ አብዲ

173

አዳማ (ኢዜአ) ህዳር 23/2015 ህዝቡ በሀገሩ ሉዓላዊነት ላይ የተቃጣውን ጦርነትና አፍራሽ ተግባር በአንድ እጁ በመመከት ለህዳሴ ግድብ ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ በመሰብሰብ የሀገር መካታነቱን በተግባር አረጋግጧል ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንትና የክልሉ የህዳሴ ግድብ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ አወሉ አብዲ ገለፁ።

የህዳሴ ዋንጫ በኦሮሚያ ክልል የነበረውን ቆይታ ማጠናቀቁን አስመልክቶ በአዳማ በተዘጋጀ መድረክ ላይ አቶ አወሉ ድጋፉ የሀገራችንን ሀብት ማልማትና መጠቀም ያስቻለን ከመሆኑም ባለፈ ከብልፅግና ጉዞ ወደ ኋላ የሚመልሰን አካል እንደሌለ ማሳያ ነው ብለዋል።

ዛሬ ዋንጫውን ወደ ሌላ ክልል ለመሸኘት ስናስብ ግድቡ በደለል እንዳይሞላና የተቀረው ግንባታ እንዲጠናቀቅ ርብርባችንን አጠናክረን ለማስቀጠል ዳግም ቃላችንን በማደስ ጭምር ነው ብለዋል።

በግድቡ ዙሪያ ሲነዛ የነበረውን አሉባልታና የኢትዮጵያ ህዝብ በግድቡ ተስፋ እንዲቆርጥ የተሸረበውን ሴራ በማክሸፍ ሦስተኛውን ዙር የውሃ ሙሌት በማጠናቀቅ የገባነውን ቃል በተግባር አሳይተናል ነው ያሉት።

የግድቡ ዋንጫ የክልሉ ቆይታና የህዝቡ የሚደነቅ የገቢ አሰባሰብ ርብርብ ትልቅ ሞራልና ወኔ ዳግም የሰነቀልን ተግባር ነው ብለዋል።

649 ሚሊዮን ብር በዋንጫው ቆይታ ለመሰብሰብ ታቅዶ 1 ቢሊዮን 48 ሚሊዮን ብር ከእቅዱ በላይ በመሰብሰብ የክልሉ ህዝብ ታሪክ መስራቱንም ተናግረዋል።

በዚህም በሀገር ላይ የተቃጣውን የህልውና ጦርነት ለመመከት በሚደረገው ጥረት ግንባር ቀደም ሚና ከመጫወት ባለፈ የአንድነት አርማ የሆነው የህዳሴ ግድብ ከዳር እንዲደርስ በህዝቡ፣ በአመራሩና በመላው የመንግስት ሠራተኞች ለተደረገው ርብርብ ምክትል ፕሬዚዳንቱ አመስግነዋል።

ብሔራዊ የህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ዶክተር አረጋዊ በርሔ ግድቡ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን የኢትዮጵያ ህዝብ ከ17 ቢሊዮን ብር በላይ በቦንድ ግዥና በስጦታ ድጋፍ ማድረጉን አስታውቀዋል።

እያንዳንዱ ዜጋ በግድቡ ላይ ምን አሻራ እንዳኖረ በመጠየቅ ድጋፉን ለማጠናከር ራሱን ማዘጋጀት አለበት ብለዋል።

የአንድነታችን ብርሃን የሆነው የህዳሴ ግድብ ግንባታ ከዳር እንዲደርስ በፐብሊክ ዲፕሎማሲና በህዝብ ግኑኝነት በሀገር ውስጥና በውጭ ለሰሩት አካላትና የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ምስጋና አቅርበዋል።

ለገቢ አሰባሰቡ ስኬታማነት የድርሻቸውን ለተወጡ ተቋማት ዕውቅና መሰጠቱም ተጠቅሷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም