የሰላም ስምምነቱ ፈጥነን ወደ መልሶ ግንባታና ማቋቋም እንድንገባ አስችሎናል --ርዕሰ መስተዳድሩ

102

ወልዲያ(ኢዜአ) ህዳር 23/2015  በፌደራል መንግስትና በህወሓት መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት ፈጥነን ወደ መልሶ ግንባታና ማቋቋም ስራ እንድንገባ አስችሎናል ሲሉ የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ አስታወቁ።

የክልሉ መልሶ ማቋቋም ግንባታና ገቢ ማሰባሰቢያ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር በራያ ቆቦ ወረዳ ወርቄ ቀበሌ ተካሂዷል።

ርእሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ በወቅቱ እንዳሉት በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባት ለዚህ አመት ብቻ ክልሉ 1 ቢሊየን ብር በጀት መድቧል።

ክልሉ በመደበው ገንዘብ በስምንት ዞኖች ውስጥ የመልሶ ግንባታ ስራ እንደሚጀመር ገልፀዋል።

በዞኖቹ የፈረሱ የግለሰብ ቤቶችና የአገልግሎት መስጫ ተቋማት የመልሶ ግንባታ እንደሚካሄድ ጠቁመው አገልግሎት መስጫዎች ፈጥነው ወደ ስራ እንዲገቡ እንደሚደረግ አመላክተዋል ።

በክልሉ ለሚካሄደው የመልሶ ማቋቋምና ግንባታ መርሃ ግብር የሀገሪቱ ህዝቦች፣ ረጅ ድርጅቶችና ባለሃብቶች አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

"በፌደራል መንግስትና በህወሓት መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት ፈጥነን ወደ መልሶ ግንባታና ማቋቋም ስራዎች ፊታችን እንድናዞር ያደረገን በመሆኑ ለተግባራዊነቱ ክልሉ በሙሉ ልብ ይሰራል" ሲሉ ርእሰ መስተዳደሩ አስታውቀዋል።

በጦርነቱ የወደሙ የማህበራዊ አገልግሎት ሰጭና ሌሎች ተቋማትን መልሶ ለመገንባትና ለማቋቋም በክልል ደረጃ ፅህፈት ቤት ተቋቁሞ ድርጅቶችን፣ ባለሃብቶችንና ማህበረሰቡን እያስተባበረ እንደሚገኝ የገለጹት ደግሞ በምክትል ርእሰ መስተዳድር ማእረግ የክልሉ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ አቶ ስዩም መኮንን ናቸው።

ለዘንድሮ ዓመት መልሶ ግንባታ ስራ ብቻ 12 ቢሊየን ብር ለማሰባሰብ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በሚሰበሰበው ገንዘብ ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች የጤና ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶች፣ የንፁህ መጠጥ ውሃ ተቋማት፣ የመስኖ ፕሮጀክቶችና የሌሎች አገልግሎት መስጫዎች የመልሶ ግንባታ ስራ እንደሚከናወን አመልክተዋል ።

በሰሜን ወሎ ዞን ራያ ቆቦ ወረዳ ወርቄ ቀበሌ የሙሉ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ የጤና ጣቢያ፣ የእንስሳት ክሊኒክና የመልሶ ግንባታ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ዛሬ ተከናውኗል።

በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ የክልልና የዞኑ የስራ ሃላፊዎች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላትና የአካባቢው ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም