ኮርፖሬሽኑ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ መስራት ከሚፈልጉ ሶስት ኩባንያዎች ጋር የውል ስምምነት ተፈራረመ

203

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 23/2015 የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ መስራት ከሚፈልጉ አንድ የዓለም አቀፍ እና ሁለት ሀገር በቀል ኩባንያዎች ጋር የውል ስምምነት ተፈራረመ፡፡

ስምምነቱን ከተፈራረሙት ኩባንያዎች መካከል አንደኛው "ሎንግ ማርች ኤሌክትሪካል ኢኩይፕመንት ማኑፋክቸሪንግ" የተሰኘ ኩባንያ ነው፡፡

ኩባንያው በአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ 3 ሺህ ካሬ ሜትር ሼድ በመከራየት ወደ ስራ ለመግባት የሚያስችለውን ስምምነት ከኮርፖሬሽኑ ጋር ተፈራርሟል፡፡

በዚህም ኩባንያው ከ240 ሚሊዮን ብር በላይ ኢንቨስት በማድረግ የኤሌክትሪክ ቆጣሪና ሌሎች ተያያዥ ግብዓቶችን የሚያመርት ሲሆን፤ ለ250 ዜጎች ቋሚ የስራ እድል እንደሚፈጥርም ተጠቁሟል፡፡

ሌላኛው ኩባንያ "ኤንኬ ዎርልድ ሜዲካል ኢኪዩፕመንት" የተሰኘ ኩባንያ ሲሆን፤ በቂሊንጦ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ወስጥ አንድ ሄክታር የለማ መሬት በመውሰድ ወደ ስራ መግባት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራርሟል፡፡

ኩባንያው ከ205 ሚሊዮን ብር በላይ መዋለ ንዋይ በማውጣት የህክምና ቁሳቁሶችን የሚያመርት ሲሆን፤ ከ210 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚ የስራ እድል እንደሚፈጥር ተጠቅሷል፡፡

በተጨማሪም "ዋርቃ ትሬዲንግ" የተሰኘ አገር በቀል ኩባንያ በሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ 5 ሺህ 500 ካሬ ሜትር ሼድ በመከራየት ወደ ስራ መግባት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራርሟል፡፡

ኩባንያው በተለያዩ ፓርኮች ለተሰማሩ የጨርቃጨርቅ ፋብሪካዎች ለግብዓትነት የሚውል የክር ምርት እንደሚያቀርብም ነው የተገለጸው፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ አክሊሉ ታደሰ በዚህን ወቅት፤ ኮርፖሬሽኑ አቅም ያላቸውን የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች በኢንዱስትሪ ፓርኮች ገብተው እንዲሰሩ ለማድረግ የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የውል ስምምነቱም የዚሁ ስራ አካል መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

በኢትዮጵያ ባሉ 13 ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ከ125 በላይ የውጭና የአገር ውስጥ ኩባንያዎች እየሰሩ ሲሆን፤ ኩባንያዎቹ በአጠቃላይ 81 ሺህ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል መፍጠራቸውን ከኮርፖሬሽኑ የተገኘው መረጃ ይጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም