የሰላም ስምምነቱ በኢንቨስትመንት ዘርፍ ላይ በሙሉ አቅም እንድንሰማራ እድል ይፈጥርልናል-ባለሀብቶች

118

ሀዋሳ (ኢዜአ) ህዳር 23/2015 በፌዴራል መንግስትና ህወሓት መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት በኢንቨስትመንት ዘርፉ ላይ በሙሉ አቅማችን እንድንሰማራ መልካም እድል ይፈጥርልናል ሲሉ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የሲዳማ ክልል ባለሀብቶች አስታወቁ።

በሀዋሳና በአዲስ አበባ በጤናው መስክ እየሰሩ ያሉት የሊያና ሄልዝ ኬር ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ ዶክተር ግርማ አባቢ እንዳሉት የሰላም ስምምነቱ የንግድና ኢንቨስትመንት ተሳትፏችንን እንድናሰፋ እያነሳሳን ነው ብለዋል።።

የሰላም እጦት ባለሀብቱ በተለያዩ መስኮች ተሰማርቶ እንዳይሰራ እንቅፋት ይሆንበታል ያሉት ስራ አስኪያጁ፤ አሁን የተደረሰው የሰላም ስምምነት የባለሀብቱን ስጋት እንዳቃለለ ተናግረዋል።

የጦርነትን አስከፊነትና ጉዳት ባለፉት ሁለት ዓመታት መላው ህዝብ በደንብ የተረዳው ይመስለኛል ያሉት ዶክተር ግርማ፤ መላው ህዝብ ለሰላም ስምምነቱ ተግባራዊነት ትልቅ ሀላፊነት እንዳለበት ጠቁመዋል።

የሰላም ስምምነቱ ተፈጻሚ እንዲሆን ከማድረግ አንጻር የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውንም ጨምረው ተናግረዋል።

በግብርናው መስክ የተሰማራው ሱፐር ኖቫ አግሮ ቴክ ሃላፊነቱ የተወሰነ ድርጅት ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ረደኤት ባዬ በበኩላቸው ኢንቨስትመንትና ሰላም የማይነጣጠሉና እጅና ጓንት ሆነው የሚሰሩ ናቸው ብለዋል።

የሰላም እጦት በሚያጋጥምበት ወቅት የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ይቋረጣል ያሉት ወይዘሮ ረድኤት፤ በዚህም ምክንያት የገንዘብ ፍሰት ከመቆም ባለፈ የስራ ዕድል ተጠቃሚነት እና በአጠቃላይ ሀገር ጉዳት ይገጥማታል ብለዋል።

በተለያዩ አከባቢዎች ተሰማርተው አስተዋጽኦ ለማድረግ የሚፈልጉ ሁሉ ሰላምን ቅድሚያ እንደሚያደርጉ ገልጸው፤ አሁን ላይ የተደረሰው የሰላም ስምምነት ለኢንቨስትመንቱ መነቃቃት ጉልህ ሚና ይጫወታል ብለዋል።

ሁላችንም በተሰማራንበት ለአገራችን ያለንን ለማበርከት የሰላም ስምምነቱ ተግባራዊ እንዲሆን መስራት ይገባናል ሲሉም ገልጸዋል፡፡

በወረቀት ማምረትና ህትመት ስራ የተሰማሩት አቶ ዘካርያስ ዳኜ እንዳሉት ሰላም ሲኖር ሰዎች ለመስራት ይነሳሳሉ፤ እንዲሁም የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ በበለጠ ይበረታታል ብለዋል።

የሰላም ስምምነቱ በኮሮና ቫይረስ  እና በተለያዩ ምክንያቶች ተቀዛቅዞ የቆየው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ የሚያነቃቃና በርካታ በለሀብቶችም እንዲመጡ የሚያግዝ ነው ያሉት።

ስለዚህም የሰላም ስምምነቱ ይዞ የሚመጣውን እድል በአግባቡ ለመጠቀም ሁሉም ለስኬታማነቱ የሚጠበቅበትን መወጣት አለበት ሲሉም ተናግረዋል።

ስምምነት ከተደረሰ ጀምሮ እየተሰማ ያለው ተስፋና የሚታየው መነቃቃት ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው ድርጅታቸው በቀጣይ የስራ አማራጭን በማስፋት ለመስራትና ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል ለመፍጠር ማቀዱንም አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም