የዲፕሎማሲ ስራዎችን በማጠናከር በመልሶ ማቋቋም ስራዎች ላይ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ድጋፍ እንዲያደርግ ይሰራል- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

365

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 23/2015 የዲፕሎማሲ ስራዎችን በማጠናከር መንግስት በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለማቋቋም በተጀመሩ ስራዎች ላይ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ድጋፍ እንዲያደርግ እንደሚሰራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም ዛሬ በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫ ኢትዮጵያ በፈተናዎች ውስጥ ያገኘቻቸውን የዲፕሎማሲ ድሎች ለማጽናት በትኩረት ይሰራል ብለዋል፡፡

በተለይ የአገሪቱ የገጽታ ግንባታ ላይ በትኩረት እንደሚሰራ ጠቅሰው በዚህም የኢንቨስትመንት ፍሰትን ለመጨመር ይሰራል ብለዋል።

በመንግስትና ህወሓት መካከል የሰላም ስምምነት መፈረሙን ተከትሎ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ያላት ተቀባይነት እየጨመረ መምጣቱንም ነው የተናገሩት፡፡

በዚህም የተጀመሩ የዲፕሎማሲ ስራዎችን በማጠናከር በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለማቋቋም በተጀመሩ ስራዎች ላይ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ድጋፍ እንዲያደርግ ይሰራል ነው ያሉት፡፡

ለዚህ ደግሞ በተለያዩ የዓለም አገራት ኢትዮጵያን የሚወክሉ ዲፕሎማቶችን አቅም የመገንባት ስራ በትኩረት እየተከናወነ መሆኑን አንስተዋል፡፡

በቅርቡ በመካከለኛ ደረጃ ለሚገኙ ዲፕሎማቶች የተሰጠውን ስልጠና በዚህ ረገድ ለአብነት አንስተዋል፡፡