የፀረ ሙስና ብሔራዊ ኮሚቴ ወደ ስራ በመግባት እርምጃ መውሰድ መጀመሩን አስታወቀ

177

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 23/2015 የፀረ ሙስና ብሔራዊ ኮሚቴ ወደ ስራ በመግባት እርምጃ መውሰድ መጀመሩን አስታወቀ።

በዚህም የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ በቀለን ጨምሮ በርካታ የመሬት አስተዳደር እና የፀጥታና ፍትህ ተቋማት የስራ ኃላፊዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስታውቋል።

የአገር ደህንነት ስጋት የሆነውን ሙስና ለመከላከል ብሔራዊ ፀረ ሙስና ኮሚቴ በጠቅላይ ሚኒስትሩ መቋቋሙ ይታወሳል፡፡

የኮሚቴው ሰብሳቢ እና የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተሩ ተመስገን ጥሩነህ እና የፍትሕ ሚኒስትሩ ዶክተር ጌዲዎን ጢሞቲዎስ የኮሚቴውን ስራዎች ክንውን አስመልክቶ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

በዚህም ሙስና ከኑሮ ውድነትና ስራ አጥነት ቀጥሎ የአገር ስጋት ነው ብለዋል።

በብድር አሰጣጥ፣ በፍጆታ ዕቃዎች ዘርፍ፣ ግዥና ፋይናንስ አላግባብ የመበልፀግና የሙስና ተግባራት በስፋት የሚስተዋልባቸው መሆናቸው በጥናት ተለይቷል ብለዋል።

መንግስት ሙስናን ለመከላከል በቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ጨምሮ የተለያዩ ስራዎች ሲሰራ ቢቆይም በኮሮና ወረርሽኝ እና በጦርነት ምክንያት በሚፈለገው ደረጃ ችግሩን መቅረፍ እንዳልተቻለ ተናግረዋል፡፡

ኮሚቴው የተቋቋመው የሁሉም ተቋማት መረጃ ወደ አንድ ቋት መጥቶ እንዲሰራበት በማስፈለጉ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ህብረተሰብ ያማረሩ ችግሮች በአገር ዕድገትና የብልፅግና ጉዞ ትልቅ እንቅፋት እንደሆኑ ገልፀው፣ ችግሩን ለመቅረፍ ወደ ማዕከል በማምጣት ለመከላከልና ሙሰኞችን ተጠያቂ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

እስካሁን ባለው ሂደት ህብረተሰቡ ተሳትፎ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ሶስት ንዑስ ኮሚቴ ተቋቋሞ ወደ ስራ መገባቱን ጠቅሰው፤  የመረጃ መቀበል ስርዓት መዘርጋት እንዲሁም በየተቋማቱ ጥናቶች ማሰባሰብ እርምጃዎች እየተወሰደ መሆኑን ገልፀዋል።

ዶክተር ጌዴዎን በበኩላቸው የመሬት አስተዳደር፣ የፀጥታና ፍትህ፣ ጉምሩክ፣ አገልግሎት አሰጣጥ ቅድሚያ ከተሰጣቸው ዘርፎች መሆናቸውን ገልፀው፣ በተለይ የመሬት አስተዳደር እና በፍትህና ፀጥታ ተቋማት  ላይ  እርምጃ እየተወሰደ  ነው ብለዋል።

በልማት ተነሺ ስም በሀሰተኛ ሰነድ መሬት የሰጡ ለአብነት በአዲስ አበባ ከተማ 175 ሺህ ካሬ መሬትና ከፍተኛ መጠን ያለው ሀብት የመዘበሩ፣ የኮንዶሚኒየም ቤት የመዘበሩ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር እየዋሉ መሆኑን ገልፀዋል።

በፍትህና ፀጥታ ዘርፍ ስልጣናቸውን አላግባብ በመጠቀም ከግለሰቦችና ድርጅቶች ገንዘብ የተቀበሉ አካላት በቁጥጥር ስር እየዋሉ መሆኑንም እንዲሁ።

በዚህም የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ በቀለን ጨምሮ የተለያዩ የፍትህና ፀጥታ የስራ ኃላፊዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንና የክስ ምስረታ ሂደት ላይም መሆኑን ገልፀዋል።

በቀጣይም እርምጃ የመውሰዱ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።

በአንድ ሳምንት ውስጥ ከ250 በላይ ጥቆማዎች በተለያዩ መንገዶች ቀርበው ማጣራት እየተከናወነባቸው መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

በክልሎችም ከትንሽ እስከ ከፍተኛ የተደራጀ ሌብነት ተሳታፊዎች ተጠያቂነት የማስፈኑ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም