ኢትዮጵያ በሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽነትና በልማት ለምታደርጋቸው ጥረቶች ተመድ ሙሉ ድጋፍ ያደርጋል- አንቶኒዮ ጉቴሬዝ

263

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 22/2015  ኢትዮጵያ በሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽነትና በልማት ለምታደርጋቸው ጥረቶች የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሙሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ የድርጅቱ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ገለፁ።

ለዚህም በመንግስታቱ ስር ያሉ የልማትና የተራድኦ ድርጅቶች አቅማቸውን አጠናክረው ድጋፍ እንዲያደርጉ ይሰራል ነው ያሉት።

የተመድ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዩ ጉቴሬዝ ይህን ያሉት 6ኛው የአፍሪካ ህብረት እና የተመድ ዓመታዊ ጉባዔ መጠናቀቅን በሚመለከት አዲስ አበባ ተገኝተው ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ መሀማት ጋር በሰጡት መግለጫ ነው።

በመግለጫቸውም ተመድ በአፍሪካ ሕብረት አመቻችነት ለተደረሰው የኢትዮጵያ የሰላም ስምምነት ተፈፃሚነት፣ ለመልሶ ግንባታ፣ ለሰብዓዊ ርዳታ ተደራሽነትና የመልሶ ማልማት እንቅስቃሴዎች ሙሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

የመንግስታቱ ድርጅት የአፍሪካን ችግሮች በአፍሪካ የመፍታትን ሀሳብ በፅኑ ይደግፋል ያሉት ዋና ጸሃፊው ለሰላም ስምምነቱ ተፈፃሚነትም ለአፍሪካ ሕብረት እና ለሁሉም ባለድርሻ አካላት እገዛ ያደርጋል ነው ያሉት።

በዚህም የድርጅቱ የልማትና የተራድኦ ድርጅቶች አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

የዓለም አቀፉ ማህበረሰብም በኢትዮጵያ የሚደረገውን ሰብዓዊ እርዳታ እና የመልሶ ማልማት ጥረት እንዲደግፍ ጥሪ አቅርበዋል።

የሰላም ስምምነቱ ለኢትዮጵያ ልማት፣ ለህዝቡ ሰላምና የኑሮ መሻሻል አማራጭ የሌለው ወሳኝ እርምጃ መሆኑን ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም