ኢትዮጵያና ሱዳን በሁለትዮሽና አካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ትብብር ለመጠናከር ተስማሙ

124

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 22/2015 ኢትዮጵያና ሱዳን በሁለትዮሽና አካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸው ትብብር ለመጠናከር ተስማሙ።

ስምምነት ላይ የደረሱት ዛሬ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ጄነራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን ጋር መወያየታቸውን ተከትሎ ነው።

ውይይታቸውም በሁለትዮሽና አካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ሲሆን ውጤታማ ውይይት እንዳደረጉም ተገልጿል።

አቶ ደመቀ መኮንን እና ጀኔራል አልቡርሀን ኢትዮጵያና ሱዳን በሁለትዮሽና አካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸው ትብብር እንዲጎለብት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ተቀራርበው ለመስራት መስማማታቸውም ተጠቁሟል።

የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ጄነራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን በኢትዮጵያ መንግስትና በህወሃት መካከል የሰላም ስምምነት በመፈረሙ መደሰታቸውን ገልፀው አገራቸው ለስምምነቱ አፈፃፀም ሙሉ ድጋፍ እንደምታደርግ አስታውቀዋል።

የሰላም ስምምነቱን ተግባራዊነት የሚያደናቅፉ እንደዚሁም ከሱዳን ግዛት በመነሳት በኢትዮጵያ ላይ ጥቃት ለመፈፀም የሚሞክሩ አካላትን ሱዳን እንደማትታገስ ጀኔራል አልቡርሀን አረጋገግጠዋል።

ከድንበር ጋር በተያያዘ የሚፈጠሩ ችግሮችን በኃይል ለመፍታት የሚደረግ ሙከራ ዘላቂ መፍትሄን የማያመጣ በመሆኑ ቀደም ሲል ሁለቱ አገሮች በፈረሟቸው ስምምነቶች አማካኝነት በሁለትዮሽ መስመር ለመፍታት ከመግባባት ተደርሷል።

የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብን በተመለከተ በሱዳንና ኢትዮጵያ መካከል እየታየ ያለ በጎ የትብብር መንፈስ ልዩነቱን በሦስትዮሽ መንገድ ለመፍታት ለሚደረገው ጥረት አዎንታዊ አሰተዋጽኦ እንዳለውም እምነታቸውን ገልፀዋል።

የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ጄነራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ በድንበር አካባቢ የሚስተዋሉ ህገወጥ የሰዎች፣ የጦር መሳሪያ እና የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር በጋራ ለመከላከል ተስማምተዋል።

በተያያዘም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ ከሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ጀኔራል መሀመድ ሀምዳን ዳጋሎ እና ተጠባባቂ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሊ አል-ሳዲቅ ጋርም ተነጋግረዋል።

በዚህም ወቅት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በሁለቱ አገሮች የህዝብ ለህዝብ ትስስር እንዲጠናከር ትኩረት ተሰጥቶ መሰራት እንዳለበት አስምረውበታል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ በሱዳን ርዕሰ-መዲና ካርቱም በተካሄደው የኢጋድ የሚኒስትሮች መደበኛ ስብሰባ ላይ መሳተፋቸው ይታወቃል።

የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሊ በበኩላቸው በኢትዮጵያ መንግስትና ህወሀት መካከል የሰላም ስምምነት በመፈረሙ ሱዳን መደሰቷን ገልፀው ተግባራዊየቱን አገራቸው እንደምትደግፍና አዎንታዊ ሚና እንደምትጫወት አስታውቀዋል።

ሰላም ከሌለ ልማት የማይታሰብ በመሆኑ የኢትዮጵያ ሰላም የሱዳን ሰላም እንደሆነም ጠቅሰዋል።

በካርቱም የተካሄደው የኢጋድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ እንዲሳካ ኢትዮጵያ ለዳረገችው አስተዋጽኦ እና ላሳየችው አጋርነት አመስግነዋል።

በዚህ ስብሰባ ኢጋድ አንድ ቤተሰብ እንደሆነ ማረጋገጡን ሚኒስትሮቹ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም