የክልሉ ህዝብ የአካባቢውን ሰላም በመጠበቅ የልማት ተሳትፎውን ማጠናከር አለበት-የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር

86

ጅግጅጋ (ኢዜአ) ህዳር 22 ቀን 2015  ህዝቡ የአካባቢውን ሰላም በመጠበቅ ከሌሎች እህት ወንድሞቹ ጋር በመከባበርና በመተባበር በሁሉም የልማት ዘርፍ ተሳትፎውን ማጠናከር እንዳለበት የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ ሙሁመድ አሳሰቡ።

17ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል  ህገ መንግሥቱ ያስገኛቸውን ትሩፋቶች በመዘከር ዛሬ በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ  በድምቀት ተከብሯል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅቱ፤ በዓሉ የፌዴራሊዝም ስርዓት ለሶማሌ ክልል ህዝብ ያስገኛቸውን ህገ-መንግስታዊ ጥቅሞች የሚዘከርበት ዕለት ነው ብለዋል።

ህዝቡ ከለውጡ በፊት በነበሩ ዓመታት ምስቅልቅል ሁኔታዎች ቢያጋጥመውም ቋንቋውን በመጠቀምና በመረጣቸው ልጆቹ ራሱን በራሱ እንዲያስተዳደር እድል መፍጠሩን ተናግረዋል።

የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል   መከበሩ በሀገራችንና በክልሉ የተጀመሩ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችንና የብልፅግና ጉዞ  በላቀ  ህዝባዊ ተሳትፎ ከዳር ለማድረስ መግባባቶች ለመፍጠር  እንደሚያግዝ ገልጸዋል።

ህዝቡ የአካባቢውን ሰላም በመጠበቅ ከሌሎች እህት ወንድሞቹ ጋር በመከባበርና በመተባበር በሁሉም የልማት  ዘርፍ ተሳትፎውን ማጠናከር እንዳለበበት አሳስበዋል።

የክልሉ  ምክር ቤት አፈ -ጉባኤ ወይዘሮ አያን አብዲ፤  የበዓሉ መከበር  የህዝብ ለህዝብ ትስስርን እንደሚያጠናክር ገልጸዋል።

የብልፅግና ፓርቲ የሶማሌ ክልል ጽህፈት ቤት ኃላፊ ኢንጂነር መሀመድ ሻሌ በበኩላቸው፤  ከለውጡ ወዲህ የሶማሌ ክልል  ህዝብ በሀገራዊ የፖለቲካ መድረኮች ከነበረው የዳር ተመልካችነት በመላቀቅ በፍትሃዊነት እንዲሳተፍ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ተናግረዋል።

የበዓሉ  መከበር  የክልሉን ህዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያዊን ጋር አንድነቱን ለማጠናከር እንደሚረዳ  የገለጹት ደግሞ የክልሉ ሀገር ሽማግሌዎች ተወካይ ሼህ ሙህየዲን መሀመድ ናቸው።

በዓሉን ምክንያት በማድረግ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድርና ሌሎችም በጎ ፍቃደኞች ደም ለግሰዋል።

በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የክልሉ ሀገር ሽማግሌዎች ሸንጎ አስተባባሪ ገራድ ኩልሚዬ ገራድ መከመድ፣ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ፣ ሴቶችና ወጣቶች  ጨምሮ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም