የሸኔ አሸባሪ ቡድን እኩይ ተግባር በጸጥታ ኃይሉ የጋራ ጥረት እየከሸፈ መሆኑን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ገለጸ

166

ህዳር 22/2015(ኢዜአ) በተላላኪነት በአገርና ሕዝብ ላይ ጥፋት እያደረሰ ያለውን የሸኔ አሸባሪ ቡድን እኩይ ተግባር በጸጥታ ኃይሉ የጋራ ጥረት እየከሸፈ መሆኑን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ገለጸ።

አሸባሪው ሸኔ የራሱ ዓላማ እና አጀንዳ ሳይኖረው ለጥፋት የሚልኩትን ኃይሎች ትዕዛዝ በመቀበል በአገር ላይ ጥፋት እየፈፀመና ሕዝብን ለከፍተኛ ችግር እየዳረገ ይገኛል።

አሸባሪ ቡድኑ በተለይም ከጉሙዝ ታጣቂና በጋምቤላ አካባቢ ከሚንቀሳቀስ የጥፋት ቡድን ጋር በመሆን የተለያዩ ጥፋቶችን መፈፀሙ ይታወቃል።

የሸኔ አሸባሪ ቡድን በኦሮሚያ ክልልና አጎራባች አካባቢዎች የሚያደርሰውን ጥፋትና በጸጥታ ኃይሉ ቅንጅት እየተከናወነ ያለውን ሕግ የማስከበር እንቅስቃሴ በተመለከተ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የወንጀል መከላከል ዘርፍ ኃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ጄነራል መላኩ ፋንታ ለኢዜአ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ምክትል ኮሚሽነር ጄነራሉ በማብራሪያቸው ከለውጡ ማግስት ጀምሮ የጥፋት ቡድኖች ኢትዮጵያን የቀውስ ማዕከል ለማድረግ የተለያዩ የጥፋት ሙከራዎች ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

ከጥፋት ፈጻሚዎቹ መካከል የራሱ ዓላማ እና አጀንዳ የሌለው አሸባሪው ሸኔ የጥፋት መልዕክት ተቀብሎ በአገርና ሕዝብ ላይ ጉዳት እያስከተለ መሆኑን ተናግረዋል።

ሆኖም በተላላኪነት በአገርና ሕዝብ ላይ ጥፋት እያደረሰ ያለውን የሸኔ አሸባሪ ቡድን እኩይ ተግባር በአገር መከላከያ ሠራዊትና ሌሎች የጸጥታ ኃይሎች እየከሸፈ ነው ብለዋል።

ፌደራል ፖሊስ ከአገር መከላከያ ሠራዊትና ሌሎች የጸጥታ ኃይሎች ጋር በመሆን የአገርን ህልውና እንዲሁም የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት የመጠበቅ ተልዕኮውን ለመወጣት ሌት ተቀን እየተጋ መሆኑን ኮሚሽነር ጄነራል መላኩ ገልጸዋል።

የኢትዮጵየ ፌደራል ፖሊስ አገራዊ ግዴታውን ለመወጣት በሚያስችል መልኩ መዋቅራዊ ማሻሻያ በማድረግ፣ አመርቂ ውጤቶችን እያስመዘገበ ስለመሆኑም አብራርተዋል።

በዚህም በአገርና ሕዝብ ላይ የተደቀኑ የጥፋት ሴራዎችን ከማክሸፍ በተጨማሪ የተጠናከረ እርምጃ በመውሰድ ከመከላከያና ሌሎች የጸጥታና ደኅንነት ተቋማት ጋር በቅንጅት እየሰራ ነው ብለዋል።

በከተማም ይሁን በገጠር ለግዳጅ በመንቀሳቀስ ለአገር ህልውና ሲል በጀግንነት መስዋዕትነት እየከፈለ ሲሆን ታላላቅ ተቋማትና የልማት ፕሮጀክቶችንም በመጠበቅ አደራውን እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል።

በአደረጃጀትና በተደራሽነት ለውጦችን ከማድረግ በተጨማሪ በዘመናዊ ትጥቆችና ቴክኖሎጂዎች በመታገዝ ጭምር ሌት ተቀን እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

ፌደራል ፖሊስ አገራዊ ተልዕኮውን ለመፈፀም ከሌሎች የጸጥታ ኃይሎች ጋር የሚያደርገው ቅንጅት እንዳለ ሆኖ ለስኬታማነቱ ከሕብረተሰቡ ጋር የሚያደርገው ትብብር አስፈላጊ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በመሆኑም ሕብረተሰቡ ለፖሊስ የሚያደርገውን ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም