ሀገራዊ ለውጡ የአፋር ሕዝብን ህገ-መንግሥታዊ መብቶች አረጋግጧል- የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ

174

ሰመራ (ኢዜአ) ህዳር 21/2015 ሀገራዊ ለውጡ የአፋር ክልል ሕዝብ ህገ-መንግሥታዊ መብቶች ሳይሸራረፉ እንዲረጋገጡ ማድረጉን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ አስታወቁ።

በአፋር ክልል 17ኛው የብሄር ብሄረሰበች ቀን በክልል ደረጃ በሰመራ ከተማ ዛሬ ተከብሯል።

በአከባበር ስነ ሰርአቱ ላይ የአማራና የደቡብ ክልሎች ምክር ቤቶች አፈ ጉባኤዎች፣ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ በሥነሥርዓቱ ላይ እንደገለጹት የብሄር ብሄረሰቦች ቀን በሕዝቦች የጋራ ተጋድሎ የተገኙ የሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች የድል ቀን ነው።

ከለውጡ በፊት የነበረው ኢ-ፍትሃዊ አስተዳደር ይከተለው በነበረው የይስሙላ ፌዴራሊዝም የአፋር ክልል አርብቶ አደር ህዝብ በሀገራዊ አጀንዳዎች ዙሪያ የመወሰን መብት የነፈገና አግላይ እንደነበር አስታውሰዋል።

በዚህ አግባብ ሲከበሩ የነበሩት የብሄር ብሄረሰቦች ቀን በዓሎች የእኩልነት መንፈስ የሚጎላቸው እንደነበር ገልጸዋል።

ሀገራዊ ለውጡ በፈጠረው ምቹ ሁኔታ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ እኩል የመሳተፍና የመወሰን መብት በተግባር እንዲረጋገጥ አድርጓል ብለዋል።

ይህም በሀገራችን እውነተኛ የፌዴራሊዝም ሥርዓት ተግባራዊ እንዲሆንና ብሄር ብሄረሰቦች በፓለቲካው መስክ ፍትሃዊ ተሳትፎ እንዲረጋገጥ  እድል ፈጥሯል ሲሉ ገልጸዋል።

በዚህም ዛሬ የአፋር አርብቶ አደር ልጆች ክልላቸውን በነፃነት ከማስተዳደር አልፈው በፌዴራል መንግሥቱም ውስጥ የተለያዩ ሀገራዊ ኃላፊነቶችን ወስደው በብቃት ሀገራቸውን የማገልገል እድል አግኝተዋል ብለዋል።

ከዚህም ባሻገር የአፋርኛ ቋንቋ የፌዴራል መንግሥቱም የስራ ቋንቋ እንዲሆን መወሰኑን ጠቅሰው፤ የክልሉ ሕዝብ ባህሉን፣ ቋንቋውና ታሪክ ለኢትዮጵያውያን ወንድሞቹና እህቶቹ  ለማስተዋወቅ እድል እንደፈጠረለትም ገልጸዋል።

ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ የብሄር ብሄረሰቦች ቀን በዓላት በእኩልነትና በእውነተኛ ወንድማማችነት መንፈስ እየተከበሩ እንደሚገኙም ርዕሰ መስተዳድሩ አስረድተዋል።

በዓሉን ስናከብር ወንድማማችነታችን በማጎልበት ሀገራችን የተጀመረችው የሰላምና የልማት ጉዞ እጅ ለእጅ ተያይዘን ከግብ በማድረስ ወደ ቀድሞ ከፍታዋ ለመመመለስ የገባነውን ቃል በማደስ ሊሆን ይገባል ብለዋል።

በክብረ በዓሉ ላይ የተገኙት የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ አስያ ከማል በበኩላቸው ሀገራችን ብዝሃነት በእኩልነት  የሚስተናገድባት ህብረ ብሄራዊት ሀገር መሆኗን በማረጋገጥ ነው ብለዋል።

የቋንቋ፣የባህል፣ የእምነትና ሌሎች ብዝሃነቶች ተፈጥሮ የሰጠችን ውድ ፀጋዎች መሆናቸውን አውቆ በመቀበል በብሄር ብሄረሰቦች መካከል መከባበርና ወንማማችነትን ማጠናከር ይገባል ሲሉ አስገንዝበዋል።

የአማራ ክልል የክልል ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬ በበኩላቸው ቀኑ ከዚህ በፊት ሲከበር ከነበረበት ልዩነቶችን ከሚያሰፉ የተሳሳቱ ትርክቶችና አስተሳሰቦች ተላቆ ወንድማማችነትና አብሮነትን በሚያጠናክር አግባብ መሆኑ ለሀገራዊ ግንባታው የላቀ ፈይዳ እንዳለው ገልጸዋል።

በቀጣይም የሀገራዊ አንድነታችን መሠረት የሆነውን ብዘሃነታችንን መነሻ በማድረግ የሚነዙ ጥላቻና ጥርጣሬ የሚፈጥሩ አስተሳሰቦችን እና አመለካከቶች  በፅናት መዋጋት ይገባልም ብለዋል።

የደቡብ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋጤ ሰርሞሎ በበኩላቸው ብዝሃነታችን ውበታችን ብቻም ሳይሆን የጥንካሬያችን መሠረት ነው ሲሉ ነው የገለጹት።

በመሆኑም ቀኑን እርስ በርስ ለመተዋወቅና አንድነታችን በበለጠ ለማጎልበት ተጠቅመንበት ሀገራዊ የብልፅግና ጉዟችንን ለማፋጠን ወሳኝ ታሪካዊ ምዕራፍ ላይ ነን ሲሉ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም