በሀገሪቱ አራት ክልሎች “ተደራሽ ታዳሽ ሃይል ለግብርና” ፕሮጀክቶች በሙከራ ደረጃ እየተከናወነ ነው- የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር

154

አርባ ምንጭ (ኢዜአ) ህዳር 21 ቀን 2015 በሀገሪቱ አራት ክልሎች በ6 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር “ተደራሽ ታዳሽ ሃይል ለግብርና” የተሰኙ ፕሮጀክቶች በሙከራ ደረጃ እየተከናወነ እንደሚገኝ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ገለጸ።

በሚኒስቴሩ የኢነርጂ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሱልጣን ወሊ የሚመራ ቡድን በአራት ክልሎች የተጀመሩ የፀሐይ ሃይል ፕሮጀክቶች ግንባታ ሂደትን እየጎበኘ ነው።

በጉብኝቱ ወቅት ሚኒስትር ዲኤታው ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ መንግስት የኢትዮጵያን የሃይል ፍላጎት የተለያዩ አማራጮች በመጠቀም ለማሟላት በትኩረት እየሰራ ነው።

ሀገሪቱ ያላትን የውሃ ሀብት ተጠቅማ ትላልቅና መለስተኛ የሀይል ማመንጫ ግድቦች በመገንባት የህዝቡን ፍላጎት ለመሸፈን መታቀዱን አመልክተዋል።

ከሚገነቡትም ውስጥ በሂደት ላይ ያሉት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብና ኮይሻ ሀይድሮ ኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጫ የጠቀሱት ሚኒስቴር ዴኤታው፤ እነዚህ ሲጠናቀቁ የሀገር ውስጥ የሀይል ፍላጎት በማሟላት ወደ ውጭ በመላክ የኢኮኖሚ ምንጭ ለማሳደግ እንደሚረዱ አስረድተዋል።

በብሔራዊ የኤሌክትሪፍኬሽን ፕሮግራም የውሃ ታዳሽ ሃይል ተደራሽ ለማድረግ እየተከናወነ ያለው እንዳለ ሆኖ በተጓዳኝ ከጸሐይ የሚገኝ ሃይል ለማዳረስም እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ለዚህም ከአፍሪካ ልማት ባንክና ለጋሽ ድርጅቶች በተገኘ 6 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በአራት ክልሎች “ተደራሽ ታዳሽ ሃይል ለግብርና” የተሰኘ ፕሮጀክት በሙከራ ደረጃ እየተከናወነ ይገኛል ነው ያሉት።

በዝናብ ላይ የተመሠረተ ግብርና ሀገራችንን የትም አያደርሳትም ያሉት ዶክተር ሱልጣን፤ ፕሮጀክቱ ህብረተሰቡን የሃይል ተጠቃሚ ከማድረግም በላይ በመስኖ ልማት ምርትና ምርታማነት ለመጨመር እንደሚያግዝ አመላክተዋል።

በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብና ሲዳማ ክልሎች ከአራት ወር በፊት የተጀመረው ይሄው ፕሮጀክት በሁለት ዓመት ተኩል ውስጥ ሲጠናቀቅ ከሰባት ሺህ በላይ ዜጎችን የሃይል ተጠቃሚ ያደርጋል ብለዋል።

ከዚህ ባሻገር 1 ሺህ 325 ሄክታር መሬት በመስኖ ማልማት እንደሚያስችል ዶክተር ሱልጣን ጠቁመዋል።

ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴርና ከአግሪካልቸራል ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት የተውጣጡ አባላት ያሉት ቡድን በአራቱም ክልሎች የሚገኙ ፕሮጀክቶችን ተዟዙረው እየጎበኙ ይገኛሉ።

በጉብኙቱ ከተካተቱት ፕሮጀክቶች መካከል በደቡብ ክልል ጋሞ ዞን የአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ የሚገኘው አንዱ ነው።

የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ቃፌ ቃፍሬ ፤ ፕሮጀክቱ ወደ ተግባር ከገባ አራት ወራት ማስቆጠሩን ጠቅሰው፤ ህዝቡ ለዘመናት ሲያነሳው የነበረው የኤሌክትሪክ ሃይል ፍላጎት ጥያቄ ይመልሳል ብለው እንደሚጠብቁ ገልጸዋል ።

በአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ የሞርቼ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር መለሰ ደፈርሻ በሰጡት አስተያየት፤ ቀበሌው የኤሌክትሪክ ሀይልም ሆነ ንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር ያለበት መሆኑን ተናግረዋል።

አሁን ላይ በቀበሌያቸው የመጣው ይህ ፕሮጀክት ተጠናቆ ወደስራ ሲገባ የኤሌክትሪክ ሀይል ከማግኘት ባለፈ በመስኖ ልማት ተጠቃሚ እንሆናለን ብለው እንደሚጠብቁ ገልጸዋል።

ለዘመናት ስናነሳው ለነበረው ጥያቄ የሚመልስ በመሆኑ ደስታችን ወደር የለውም ያሉት አርሶ አደሩ፤ ለፕሮጀክቱ ተፈጻሚነት የበኩላቸውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።

ፕሮጀክቱን በቀጣይም ወደ ሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች አስፋፍቶ በመተግበር ብሔራዊ የኤሌክትሪፍኬሽን ፕሮግራም ለማሳካት እንደሚሠራ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አመልክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም