አገራዊ የምክክር ሂደቱን የተሳካ በማድረግ ለአገር ዘላቂ ሰላምና ልማት መስራት የሁሉም ታሪካዊ ኅላፊነት ሊሆን ይገባል- አፈ-ጉባዔ ታገሰ ጫፎ

236

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 21/2015 አገራዊ የምክክር ሂደቱን የተሳካ በማድረግ ለአገር ዘላቂ ሰላምና ልማት መስራት የሁሉም ታሪካዊ ኅላፊነት ሊሆን እንደሚገባ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ ገለጹ።

ከተቋቋመ ዘጠኝ ወራት ያስቆጠረው የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን የእስካሁን ስራና የቀጣይ ዐበይት ክንውኖችን የተመለከቱ ሪፖርቶችን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቧል።

የምክር ቤቱ አባላት በቀረበው ሪፖርት ኢትዮጵያዊያንን ያላግባቡ መሰረታዊ ችግሮችን በምክክር ለመፍታትና አገራዊ መግባባት ለመፍጠር ግብ የያዘው ኮሚሽን ስራዎች ትልቅ ተስፋ ማንገባቸውን መረዳታቸውን ተናግረዋል።

በምክክር ሂደት የተሳታፊዎች ልየታ፣ የውይይት ቦታዎችን የማቀናጀት፣ ከሚዲያና ኮሙኒኬሸን፣ ከፀጥታ፣ ከተደራሽነትና አካታችነት አንጻር ምክክሮቹ እንዴት ይከናወናሉ ሲሉ ሃሳቦችን አንስተዋል።

በተለይም አካታችነት፣ አሳታፊነት፣ ገለልተኝነት እና ነጻነትን በተመለከተ በጥንቃቄና ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ባሳተፈ አግባብ በምን መልኩ ይከናወናል ሲሉ ጠይቀዋል።

የምክክር ኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ አካታችነት፣ ግልፅነትና አሳታፊነት በኮሚሽኑ መቋቋሚያ አዋጅ የተደገነገ ስለመሆኑና የአጀንዳ ልየታና የውይይት ሂደቱም ሁሉንም በሚያሳትፍ አግባብ እንደሚከወን አረጋግጠዋል።

በመሆኑም የሴቶችን እና አካል ጉዳተኞችን አሳታፊነት ጨምሮ ሁሉንም ህብረተሰብ ክፍል በማሳተፍ እኩል ተደማጭነት ይኖራል ብለዋል።

ከኢትዮጵያ ውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያንም በአገራዊ ምክክር ሂደቱ ባለድርሻ ሆነው ይሳተፋሉ ነው ያሉት።

የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ስትራቴጂ ቀረፃ እየተጠናቀቀ በመሆኑ ኮሚሽኑ ዝርዝር ሂደቶችን በተመለከተ የተግባቦት የሚዲያ ስራዎችን በአግባቡ እንደሚሰራም ገልጸዋል።

በዚህ ሂደትም የምክር ቤት አባላት ለተግባራዊነቱ ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባቸው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ፤ ምክክሩ አካታችነት፣ ነፃነትና ተዓማኒነትን በተግባር የሚያረጋገጥ መሆኑን ገልጸዋል።

ኮሚሽኑ በሶስት ዓመታት ውስጥ የተሰጠውን የጊዜ ገደብ በመጠቀም በመሰረታዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት እና የዴሞክራሲ መደላድል የመፍጠር ግቡን ያሳካል ብለዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ፤ በተያዘው የ2015 በጀት ዓመት ቁልፍ ተግባራት መካከል አንዱ ሀገራዊ የምክክር ሂደቱ መሆኑን ተናግረዋል።

ሀገራዊ ምክክሩን ማሳካት ከቻልን፣ ጸጋ ኖሯት በተቸገረች አገር ለሚኖረው ቀጣይ ትውልድ ትልቅ ውለታ እንደሆነ ገልጸው፤ ለስኬታማነቱ ድጋፍ መስጠት የሁሉም ታሪካዊ ሃላፊነት እንደሆነ ተናግረዋል።

ምክክር ኮሚሽኑ በመሰረታዊ አገራዊ ጉዳይ የጋራ አቋም ላይ ለመድረስ ግብ እንደተያዘ ገልጸው፤ ምክክሩ በአጀንዳዎች ላይ የሚደረግ ወይም የልሂቃንና ፖለቲከኞች ሳይሆን ህዝቡ በነቂስ የሚሳተፍበት እንደሆነ ተናግረዋል።

በአጀንዳ ልየታው የውይይት ሂደት የተሰበሰቡ አጀንዳዎች ተለይተው በምክክር አቋም ይወሰድባቸዋልም ነው ያሉት።

የምክክር ሂደቱ ዲዛይን በተደረገ መልኩ የሚከወን በመሆኑ የተወሳሰበ የአጀንዳ ችግር እንደማይፈጠር ገልጸው፤ የምክር ቤት አባላት ለምክክር ሂደቱ ስኬት በንቃት መሳተፍና መደገፍ እንደሚገባቸው ጠቁመዋል።

ሀገራዊ ምክክሩ ካለምንም የውጭ ኅይሎች ጫና በገለልተኝነትና በነፃነት በመሆኑ ለስኬታማነቱ መደገፍ እና የምክክር ውጤቱን ውሳኔ ለማክበርና ለመቀበል ዝግጁ መሆን እንደሚገባ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የቀጣይ ዐቢይ ተግባራትን የክንውን ጊዜ ሰሌዳ ዛሬ ይፋ አድርጓል።

በዚህም እስከ ታህሳስ 2015 ዓ.ም የአሰራር ስርዓት መዘርጋት፣ በጥርና የካቲት ወራት አጀንዳ ማሰባሰብ፣ ከየካቲት እስከ መጋቢት 2015 ዓ.ም የምክክር አጀንዳዎችን ቀረፃ ማጠናቀቅ እንዲሁም በመጋቢት 2015 ዓ.ም ሀገራዊ ምክክሮች ይከናወናሉ ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም