የቴክኒክና ሙያ የትምህርት ተቋማት የፈጠራ ስራዎች የሀብት ምንጭ እንዲሆኑ እየተሰራ ነው- የሥራና ክህሎት ሚኒስትር

241

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 21/2015 የቴክኒክና ሙያ የትምህርት ተቋማት የፈጠራ ስራዎች ችግር ፈቺና ለፈጣሪዎቹም የሀብት ምንጭ እንዲሆኑ እየተሰራ መሆኑን የሥራና ክህሎት ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል ተናገሩ።

15ኛው ዓለም አቀፍ ኢንተርፕርነርሺፕ ሳምንት” ሚሊዮን ፈተናዎች፣ ሚሊዮን ዕድሎች” በሚል መሪ ሃሳብ መካሄድ ጀምሯል፡፡

የሥራና ክህሎት ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል፤ በመርሃ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ስራ ፈጣሪነትን ከክህሎት ልማት ጋር ለማቀናጀት የሚያስችሉ ስራዎች በመከናወን ላይ ይገኛሉ ብለዋል።

የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ተቋማት በርካታ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ውጤቶች በማፍለቅ ረገድ እያበረከቱ ያሉት አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው ፈጠራዎቹ ችግር ፈቺ እና የሃብት ምንጭ እንዲሆኑ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ችግር ፈቺ ከማድረግ ባለፈ ለፈጣሪዎቹ የሀብት ምንጭ እንዲሆኑ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አክለዋል፡፡

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ዴኤታ ንጉሱ ጥላሁን በበኩላቸው በፕሮግራሙ ከኢንተርፕረነርሺፕ ጋር የተያያዙ ልዩ ልዩ ሁነቶች እንደሚከናወኑ ተናግረዋል፡፡

ለአብትም በቴክኖሎጂ እና በቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች የተዘጋጁ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ውድድር፤ኤግዚቢሽንና ልምድ ልውውጥ፤ ከስራ ፈጠራ ጋር ተያይዞ የተዘጋጁ አውደ ጥናቶች ቀርበው ውይይት ይካሄድባቸዋል ብለዋል፡፡

አያይዘውም ለዘርፉ ማደግ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት እውቅናና ለኢንተርፕራይዞች የማበረታቻ ሽልማት የሚሰጥባቸው መርሀ ግብሮች እንደሚኖሩ ጠቅሰዋል፡፡

የቀኑ መከበር ዋነኛ ዓላማም ኢንተርፕረነርሺፕ በህብረተሰቡ ዘንድ ትኩረት እንዲያገኝ፤ የዜጎችን ችግር ፈቺ አስተሳሰብ ለማጎልበትና ሙያዊ ስነ ምግባር እንዲላበሱ ለማብቃት ያለመ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የመጡ ስራ ፈጣሪዎች የቴክኖሎጂ የፈጠራ ስራዎቻቸውን ለማቅረብ መቻላቸው እንዳስደሰታቸው ገልፀዋል።

መድረኩም በስራ ፈጣሪዎች መካከል የልምድ ልውውጥ ለማድረግና፤ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር የገበያ ትስስር ለመፍጠር በር ይከፍታል ብለዋል፡፡

መንግስት የሀገር ውስጥ የፈጠራ ስራዎችን በስፋት መደገፉ ኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ከውጭ ለማስገባት የምታወጣውን የውጭ ምንዛሬ ለመቀነስ የሚያግዝ በመሆኑ ዘርፉን በትኩረት እንዲደግፍ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም