ለሰላም ስምምነቱ ስኬታማነት የድርሻችንን ለመወጣት ዝግጁ ነን ---የአማራ ክልል ምክር ቤት አባላት

123

ባህር ዳር (ኢዜአ) ህዳር 21 ቀን 2015 በፌዴራል መንግስትና በህወሃት መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት ስኬታማ እንዲሆን የድርሻቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን የአማራ ክልል ምክር ቤት አባላት ገለጹ።

የምክር ቤቱ አባል የሆኑት አቶ ጌትነት ተስፋ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ለሀገር ሁለንተናዊ ዕድገትና ለህዝብ ደህንነት ለሰላም የሚከፈል ዋጋ መተኪያ የለውም።

ባለፉት ሁለት ዓመታት በነበረው ጦርነት ሰብአዊና ቁሳዊ ውድመት በመድረሱ ዜጎች ለስደትና ለከፋ ችግር እንዲጋለጡ ማድረጉን አስታውሰዋል።

የነበረው ችግር ታልፎ አሁን ሰላም መምጣቱ የሚደገፍ መሆኑን ጠቅሰው፤ የተደረሰው የሰላም ስምምነት ከዳር እንዲደርስና በትክክል ታች ድረስ እንዲተገበር የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል።

የህዝቡ ሰላም በዘላቂነት እንዲረጋገጥና ወደልማቱ እንዲመለስ፣ የወደሙ መሰረተ ልማቶች መልሰው እንዲገነቡና ቤት ንብረታቸው የወደመባቸው ዜጎች በዘላቂነት እንዲቋቋሙ የአቅማቸውን እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

ሌላዋ የምክር ቤቱ አባል ወይዘሮ አስናቀች ኃይሌ በበኩላቸው በነበረው ጦርነት ህዝቡ በርካታ ፈተና ማየቱን አስታውሰዋል።

በመንግስት የተደረሰው የሰላም ስምምነት በትክክል እንዲተገበር ህብረተሰቡ ስለሰላሙ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው የምክር ቤት አባላት በየተመረጡበት አካባቢ ህዝቡን የማወያየትና የማስገንዘብ ስራ እየሰሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

በጦርነቱ የተጎዳውን ማህበረሰብ የመለየት ስራ በመሰራቱም ቤት ንብረታቸው የወደመባቸው ወገኖች መልሰው እንዲቋቋሙ ለማድረግ እየሰሩ መሆናቸውን አመልክተዋል።

''ሰላም ለሁሉም ነገር መሰረት ነው'' ያሉት ሌላኛው የምክር ቤት አባል አቶ ሃውልቱ መኮነን፤ ጦርነት ምን ያህል አስከፊ እንደሆነ ጥልቅ የሆነ ግንዛቤ ኖሮት ሁሉም ለሰላሙ ዘብ እንዲቆም የማስገንዘብ ስራ በትኩረት እንደሚሰሩ ጠቅሰዋል።

በጦርነቱ የወደሙትን መሰረተልማቶች መልሶ ለመገንባትና የተፈናቀሉ ዜጎችን በዘላቂነት ለማቋቋም ለሚደረገው ጥረትም ህብረተሰቡን በማስተባበር የድርሻቸውን እንደሚወጡ አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም