በፍኖተ ካርታው ህጻናት የአፍ መፍቻቸውን ጨምሮ ሦስት ቋንቋዎችን እንዲማሩ መታሰቡ አቅማቸውን ያላገናዘበ ነው---የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን

73
መቀሌ መስከረም 17/2011 በአዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ ዝግጅት ረቂቅ ጥናት ህጻናት የአፍ መፍቻ ቋንቋቸውን ጨምሮ ሦስት ቋንቋዎችን እንዲማሩ የሰፈረው ሀሳብ ዕድሜያቸውን ያላገነዘበ ነው ሲሉ የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ። የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ መምህራንና ሠራተኞች በረቂቅ ጥናቱ ላይ ውይይት አድርገዋል። በፍኖተ ካርታው ከቅድመ መደበኛ ትምህርት ጀምሮ እስከ ትምህርት ፖሊሲው በቀረቡ አጀንዳዎች ላይ ምሁራኑ የተለያዩ ሃሰቦችና ጥያቄዎች በማንሳት ተወያይተዋል፡፡ ምህራኑ በእዚህ ወቅት እንዳሉት ፍኖተ ካርታው ህጻናት ሊማሩት የታሰበውን የአፍ መፍቻ ቋንቋ ጨምሮ አማርኛ፣ እንግሊዝኛና ሌላ የጎረቤት ክልል ቋንቋ እንዲማሩ በሚል የተቀመጠው ሀሳብ ዳግም ሊጤን ይገባል። "በፍኖተ ካርታው በገጠርና በከተማ በሚገኙ መዋዕለ ህጻናት የሚሰጠው ትምህርት ሁለት ዓመት እንዲሆን የተቀመጠው መልካም ጎን ቢኖረውም በደረጃው ትምህርቱን ለመስጠት የተመቻቸ ሁኔታ የተቀመጠበት ሁኔታ ባለመኖሩ እንዴት ተግባራዊ ይሆናል" የሚል ጥያቄም በምሁራኑ ተንጸባርቋል። "ዕድሜው ለትምህርት የደረሰ ህጻን በስድስት ዓመቱ ትምህርት ይጀምራል" የሚለውም ከብዙ ነባራዊ ሁኔታ ጋር ተገናዝቦ ዳግም መታየት እንዳለበትም የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አባላት ሀሳብ አንስተዋል፡፡ "እስከ 8ኛ ክፍል በአፍ መፍቻ ቋንቋ ትምህርት ይሰጥ የነበረው በፍኖተ ካርታው ዝግጅት ረቂቅ ጥናት ላይ ወደ 6ኛ ክፍል ዝቅ እንዲል መደረጉ ብዙ የሚያስኬድ ባለመሆኑ እንደነበረው ቢቀጥል የተሻለ ይሆናል" ሲሉም አስተያየት ሰጥተውበታል። ምሁራኑ በተጨማሪም " በፍኖተ ካርታው የስምንተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በሀገር ደረጃ ይዘጋጃል የሚለው የክልሎችን ስልጣን የሚጋፋ ነው" በሚል ሀሳባቸውን ገልጸዋል። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት መልቀቂያ ፈተና 10ኛ ክፍል ከመሆኑ ይልቅ 12ኛ ክፍል እንዲሆን የተቀመጠውን በመልካም ጎኑ እንዳዩት የገለፁት ምሁራኑ በደረጃው የሚሰጠው ትምህርት ከቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ጋር ይሰጣል በሚል የሰፈረው ሀሳብ  በተመለከተ ግልጽ አይደለም "በማለት ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የማህበራዊ ሳይንስ ትምህርቶች የሚፈጁት የስልጠና ጊዜ  ከሦስት ወደ አራት ዓመት ከፍ እንዲል መደረጉ አሳማኝ ምክንያት እንደሌለውም  ምሁራኑ በውይይታቸው ወቅት አንስተዋል፡፡ "የሁለተኛ ደረጃ መምህራን ምድባና ዝውውር በትምህርት ሚኒስትር ይተዳደራል" የሚለው ያልተማከለ አስተዳደር ወደ ማዕከላዊ አስተዳደር የሚውሰድ በመሆኑ ዳግም እንዲታይ ጠይቀዋል፡፡ "የመምህራን ዝውውሩ የመምህራንን ፍላጎትና ችግር ግምት ውስጥ ያስገባ ባለመሆኑ ቢታሰብበት ይገባል" ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል ። ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል መምህር አማኑኤል አብርሃ  እንዳሉት የፍኖተ ካርታው ዝግጅት ሕብረተሰቡ ተወያይቶበት ተጨማሪ ሀሳብ ቢታከልበት ይበልጥ ግብአት ለማግኘት ያስችላል፡፡ "ጊዜ ተወስዶ በተጨማሪ አስተያየቶች ቢዳብርና ለቀረቡ ጥያቄዎች ምላሽ አየተሰጠበት ቢካሄድ ኖሮ የጋራ መግባባት ላይ ይደረስ ነበር" ብለዋል።፡ "ለቀረቡ ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጥ አካል ባለመኖሩ ሀሳቦች እንደሚፈለገው አልተንሸራሸሩም" ያሉት ደግሞ የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ  መምህር ብርሃኑ ገብረመድህን ናቸው፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም