አገራዊ ፕሮጀክቶችን በራስ ከሚገኝ ገቢ የመገንባት አቅሙን እያሳደገ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ገለጸ

157

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 20 ቀን 2015 አገራዊ ፕሮጀክቶች በገንዘብ እጥረት ሳቢያ እንዳይጓተቱ በራስ ከሚገኝ ገቢ የመገንባት አቅምን እያሳደገ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ።

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የፋይናንስ ዘርፍ ሥራ አስፈጻሚ ደመረ አሰፋ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ተቋሙ የኃይል አቅርቦት ፍላጎትን ለማሟላት የተለያዩ ፕሮጀክቶችን እየገነባ ነው።

ለፕሮጀክቶቹ ግንባታ ከብድር፣ ከድጋፍና ከቦንድ ሽያጭ ከሚያገኘው ገንዘብ በተጨማሪ ፕሮጀክቶችን በራስ ገቢ ለመሸፈን በትኩረት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት የኃይል ማመንጫና ማከፋፈያ ጣቢያዎችን ጨምሮ የተለያዩ ፕሮጀክቶች በፋይናንስ እጥረት ሳቢያ እንዳይጓተቱ ተቋሙ ከፍተኛ ርብርብ እያደረገ መሆኑንም አንስተዋል።

ተቋሙ ለአገር ውስጥና ለውጭ ከሚያቀርበው ኃይል ሽያጭ የሚያገኘው ገቢ ለፕሮጀክቶች ግንባታ እንዲውል በማድረግ የተሻለ አቅም እንዲኖረው እያደረገ መሆኑንም አብራርተዋል።

ይህም ተቋሙ ከጊዜ ወደ ጊዜ ፕሮጀክቶችን በራሱ አቅም ለመሸፈን የሚያስችለው እድል እንዲኖር የሚያደርግ መሆኑን ነው የገለጹት።

ለአብነት የባህርዳር-ወልድያ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ግንባታ በተቋሙ ወጪ ተሸፍኖ እየተገነባ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ከዚህ በፊትም የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎችና ማስተላለፊያዎች ተገንብተው ሥራ መጀመራቸው ከተገኙ ውጤቶች መካከል እንደሚጠቀስ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ለሱዳን እና ጂቡቲ በሙከራ ደረጃ ደግሞ ለኬንያ ኃይል እያቀረበች መሆኑን ያስታወሱት አቶ ደመረ፤ ይህም የአገራቱን የልማት ትስስር ለማጠናከር እየረዳ መሆኑን ይገልጻሉ።

ተቋሙ ካሁን በፊት በዓመት ከ3 ቢሊየን ብር ያልበለጠ ገቢ ከተለያየ መንገድ ያገኝ እንደነበር ጠቁመው አሁን ላይ ገቢው እያደገ በመምጣቱ በዘንድሮው ዓመት ብቻ 25 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም