ባለፉት አሥር ዓመታት በአፍሪካ የሳይበር ጥቃት 20 ቢሊየን ዶላር የገንዘብ ኪሳራ ማድረሱን ጥናት አመለከተ

118

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 20 ቀን 2015 ባለፉት አሥር ዓመታት በአፍሪካ 873 ሚሊየን የሳይበር ጥቃቶች የተደረጉ ሲሆን 20 ቢሊየን ዶላር የገንዘብ ኪሳራ ማድረሱን ጥናት አመለከተ።

በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት ከሚካሄደው 17ኛው ዓለም አቀፍ የበይነ-መረብ አስተዳደር ጉባዔ ጎን ለጎን ጉባዔውን የተመለከቱ ውይይቶችና ሪፖርቶች እየቀረቡ ነው።

በተባበሩት መንግሥታት ኢኮኖሚክ ኮሚሽን እንደ አውሮፓውያን ዘመን አቆጣጠር ከ2011 እስከ 2021 በኢንተርኔት ተደራሽነትና የሳይበር ተጋላጭነት ላይ የተደረገ የጥናት ውጤት ቀርቧል።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሳይበር ደኅንነት ልማትና የኢንዱስትሪ አብዮት አማካሪ ዶክተር ጂምሰን ኦሉፉዬ የጥናቱን ውጤትና ምክረ-ሀሳቦችን አቅርበዋል።

ጥናቱ 40 የአፍሪካ አገሮችን ጨምሮ በኢሲያና ላቲን አሜሪካ ላይ የተደረገ መሆኑን አብራርተዋል።

ጥናቱ በዓለም ዘላቂና ደኅንነቱ የተጠበቀ ምጣኔ ሀብትን ለማስቀጠል፣ በአፍሪካ ልማትን ለማፋጠን የሳይበር ደኅንነትን ማረጋገጥ ያለውን ፋይዳ ዳሷል።

ጥናቱ በተደረገባቸው ዓመታት በአፍሪካ የተደረጉ የሳይበር ጥቃቶችና የደረሰው የገንዘብ ኪሳራን በሪፖርቱ ተመልክቷል።

በዚህም 873 ሚሊየን የሳይበር ጥቃቶች ሲፈጸሙ 20 ቢሊየን ዶላር የፋይናንስ ኪሳራ አድርሷል ብለዋል።

ጥናቱ ኢንተርኔት የዓለምን ምጣኔ ሀብትና ማህበራዊ እንቅስቃሴ የሚያቀላጥፉ ቢሆንም ጠንካራ የአስተዳደር ሥርዓት ካልተዘረጋለት የሚያደርሰው ቀውስ እየጨመረ እንደሚሄድ በመጠቆም የመፍትሔ አቅጣጫዎችን አመላክቷል።

ጠንካራና ተጠያቂ ተቋማትን መገንባት፣ በሚፈጸሙ የሳይበር ጥቃቶችና በሚደርሱ ኪሳራዎች ላይ ተጠያቂ የሚያደርጉ ጠንካራ ሕጎችን ማውጣትና መተግበር በመፍትሔነት ከተመላከቱት ውስጥ ይጠቀሳሉ።

ይሁን እንጂ የሳይበር ደኅንነት ጉዳይ የዓለም መንግሥታት የፖሊሲ ጉዳይ በመሆኑ የሁሉንም ትብብር የሚጠይቅ በተለይም የተባበሩት መንግሥታት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ኮሚሽን ለጉዳዩ ትልቅ ትኩረት መስጠት እንዳለበት ጥናት አቅራቢው ጠቁመዋል።

በበይነ-መረብ አስተዳደርና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ እየተካሄደ የሚገኘው የዓለም የበይነ-መረብ አስተዳደር ጉባዔ ነገም ይቀጥላል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም