የአማራ ክልልን መስህቦች በማልማት የቱሪዝም ዘርፉን እናሳድጋለን...የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ

186
ደሴ መስከረም 17/2011 የአማራ ክልልን የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ መስህቦች በማልማት ከዘርፉ ሊገኝ የሚገባውን ጥቅም ለማሳደግ የሚያስችሉ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ። ዓለም አቀፉ የቱሪዝም ቀን በክልል ደረጃ በግሸን አምባ ላይ ትናንት ምሽት ተከብሯል፡፡ የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሂሩት ካሳው በእለቱ “ዓለም አቀፉን የቱሪዝም ቀን ከመስቀል በአል ጋር በማገናኘት በመስቀለኛው ታራራና የክርስቶስ ግማደ መስቀል ተገኝቶበታል ተብሎ በሚታመነው ግሸን ደብረ ከርቤ  መከበሩ ቅርሱን ለማስተዋወቅ የሚያግዝ ነው”ብለዋል፡፡ ክልሉ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ መስህቦች መገኛ መሆኑን የጠቆሙት ዶክተሯ በሚፈለገው ደረጃ ባለመልማቱ፣ የማስተዋወቅ ስራው ውስን በመሆኑና አስፈላጊ መሰረተ ልማት ባለመሟላቱ ከዘርፉ መገኘት ያለበትን ጥቅም እንዳላስገኘ ገልጸዋል፡፡ “መንግሥትና ቢሮው በክልሉ ቀጣይነት ያለው የቱሪዝም እንቅስቃሴ እንዲኖር ትኩረት ሰጥተው ይሰራሉ” ያሉት ኃላፊዋ ወደ ግሸን ደብረ ከርቤ የሚያደርሰውን 17 ኪ.ሜ አስቸጋሪ መንገድ በሁለት ዓመት ውስጥ በአስፋልት ለመሸፈን በቅርቡ ጨረታ እንደሚካሄድም አረጋግጠዋል፡፡ ክልሉ ያሉትን ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ መስህቦች በበማልማትና በማስተዋወቅ ዘርፉን ትርፋማ ለማድረግ አስፈላጊው ስራ እንደሚከናወንም ገልጸዋል። የዞኑ ባህል ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ ኢያሱ ዮኃንስ እንዳስታወቁት ዞኑ በርካታ ተንቀሳቃሽና ቋሚ፣ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ቅርሶች ቢኖሩትም በሚገባው መልኩ አልተዋወቁም፡፡ ከነዚህ ቅርሶች ውስጥ አንዱ የሆነው ግሸን ደብረ ከርቤ ማርያም እምቅ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ መስህቦች የሚስተዋሉበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ “በተለይ አምባው በተፈጥሮው የመስቀል ቅርጽ ያለው ተራራ የሚገኝበትና ክርስቶስ የተሰቀለበት ግማደ መስቀል ያለበት በመሆኑ አካባቢውን ለዓለም ቅርስነት የሚያበቃ ነው” ብለዋል። ከዚህ በተጨማሪም በዚህ ስፍራ ሌሎች አካባቢዎች የማይገኙ ታሪካዊ መጽሓፍት ቦታውን ለተመራማሪዎችና ለቱሪስቶች ከፍተኛ መስህብ እንደሆነም አስረድተዋል። በመሆኑም በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ መምሪያው ካለፈው ዓመት ጀምሮ የጽሁፍና የምስል መረጃዎችን ያሰባሰበ ሲሆን በዚሁ ዓመት ጥናቱ ተደራጅቶ ለቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን እንደሚቀርብ ተናግረዋል። የግሸን ደብረ ከርቤ ማርያም ቤተክርስቲያን ዋና አስታዳዳሪ መምህር ቆሞስ አባ ለይኩን ወንድይፍራው በበኩላቸው እንደገለጹት የዓለም የቱሪዝም ቀን በክልል ደረጃ በግሸን አምባ መከበሩ አካባቢውን ከማስተዋወቅ ባለፈ ወደ ስፋራው የሚመጣውን ህዝብ ቁጥር እንዲጨምር ያስችለዋል፡፡ በአገሪቱ የተጀመረው ለውጥ የፈጣሪ ፍቃድ ያለበትና የህዝቡ ንቁ ተሳትፎ የተስተዋለበት በመሆኑ ሁሉም ሊጠብቀው እንደሚገባ አሳስበው በአንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋሉ ችግሮች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ቤተክርስቲያን የሸምጋይነት ሚናዋን እንደምትወጣ አረጋግጠዋል፡፡ በበዓሉ ላይ የተገኙትና ከ40 መታት በኋላ ወደ አገሬ መጥቻለሁ ያሉት አቶ ሰለሞን ያለለት በአንፃሩ በሰላም እጦት ምክንያት ጥለዋት የሄዱት ሀገራቸው በተረጋጋ ሰላምና አንጻራዊ ዴሞክራሲ ውስጥ ሆነው በማግኘታቸው ደስታቸው እጥፍ ድርብ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ሀገር ሰላም ከሆነና ዴሞክራሲ ከተረጋገጠ በውጭ ያለ ኢትዮጵያዊ እውቀትና ሃብቱን ለአገሩ ልማት የሚያውልበት እድል ሰፊ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ሰሎሞን እሳቸውም በአዋጭ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ለመሰማራት የዳሰሳ ጥናት በማድረግ ላይ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ሽግግር ለቱሪዝም ልማት በሚል መሪ ሃሳብ የተከበረውን ዓለም አቀፉ የቱሪዝም ቀን በክልል ደረጃ ሲከበር ከ30 ሺህ የሚልቅ ህዝብ ተከታትሎታል፡፡          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም