ኢራንና አሜሪካ ዛሬ በኳስ ሜዳ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ሆኗል

390

አዲስ አበባ ሕዳር 20/ 2015 (ኢዜአ) በኳታር አስተጋጅነት እየተካሄደ በሚገኘው 22ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ በምድብ ሁለት ኢራንና አሜሪካ ዛሬ ወደ 16 ውስጥ ለመግባት የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።

ሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች በዓለም ዋንጫው ሲገናኙ የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።22ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ዛሬ 10ኛ ቀኑን ይዟል።

40 ሺህ ተመልካች በሚያስተናግደው አል ቱማማ ስታዲየም በምድብ ሁለት ኢራን ከአሜሪካ ከምሽቱ 4 ሰአት የሚያደርጉት ጨዋታ በእግር ኳስ ቤተሰቡ በጉጉት የሚጠበቅ ነው።

ኢራን በመጀመሪያ የምድብ ጨዋታዋ በእንግሊዝ 6 ለ 2 መሸነፏ ይታወቃል።

ይሁንና በቀጣዩ ጨዋታ ዌልሰን 2 ለ 0 በማሸነፍ ወደ ጥሎ ማለፍ የመግባት ተስፋዋን አለምልማለች።

በአንጻሩ አሜሪካ በመጀመሪያ ጨዋታ ከዌልስ ጋር 1 ለ 1 ተለያይታለች።

ሁለተኛ ጨዋታዋን ከምድቡ መሪ እንግሊዝ ጋር አድርጋ ያለ ምንም ጎል አቻ ወጥታለች።

ኢራን በሶስት ነጥብ ሁለተኛ እንዲሁም አሜሪካ በሁለት ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

ኢራን ማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር የሚያሳልፋት ሲሆን አቻ ወጥታም እንግሊዝ ዌልስን ካሸነፈች 16 ውስጥ መግባቷን ታረጋግጣለች።

አሜሪካ ወደ ጥሎ ማለፍ ለመግባት ያላት ብቸኛ እድል ማሸነፍ ብቻ ነው።ኢራንና አሜሪካ በዓለም ዋንጫ ሲገናኙ ይሄኛው ለሁለተኛ ጊዜ ነው።

በፈረንሳይ አስተናጋጅነት እ.አ.አ 1998 በተካሄደው 16ኛው የዓለም ዋንጫ በምድብ ስድስት ተገናኝተው ኢራን በሀሚድ ኢስቲሊ እና ሜህዲ ማሃዳቪኪያ ግቦች 2 ለ 1 አሜሪካን ረታለች።

ብሪያን ማክብራድ ለአሜሪካ ብቸኛዋን ግብ ያስቆጠረው ተጫዋች ነበር።ሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች እ.አ.አ በ2000 በወዳጅነት ጨዋታ ተገናኝተው አንድ አቻ ተለያይተዋል።

የ45 ዓመቱ ስፔናዊ አንቲኒዮ ማቲዩ ላሆዝ የኢራንና አሜሪካን ጨዋታ በመሐል ዳኝነት ይመራሉ።

በምድብ ሁለት በአራት ነጥብ ምድቡን የምትመራው እንግሊዝ በአህመድ ቢን አሊ ስታዲየም አንድ ነጥብ ይዛ የመጨረሻ ደረጃ ከያዘችው ዌልስ ጋር ከምሽቱ 4 ሰአት ትጫወታለች።

በምድብ አንድ በከሊፋ ኢንተርናሽናል ስታዲየም አፍሪካዊቷ አገር ሴኔጋል ከኢኳዶር ከምሽቱ 12 ሰአት የምታደርገው ጨዋታ ይጠበቃል።

ሴኔጋል በሁለት ጨዋታ ሶስት ነጥብ የያዘች ሲሆን ተጋጣሚዋ ኢኳዶር አራት ነጥብ አላት።

የቴራንጋ አንባሶች ወደ 16ት ውስጥ ለመግባት ያላቸው በቸኛ እድል ኢኳዶርን ማሸነፍ ብቻ ነው።

በአንጻሩ ኢኳዶር አቻ መውጣት ወደ ቀጣዩ ዙር ያሳልፋታል።በዚሁ ምድብ በአል በይት ስታዲየም አራት ነጥብ ያላት ኔዘርላንድስ ከምድቧ መውደቋን ያረጋገጠችውን አዘጋጅ አገር ኳታርን ከምሽቱ 12 ሰአት ትገጥማለች።