የሌማት ትሩፋት ሕብረተሰቡ የተመጣጠነና ጤናማ ይዘት ያለው ምግብ እንዲያገኝና የጥምር ግብርናን የሚያበረታታ መሆኑ ተገለጸ

142

ጅማ (ኢዜአ) ህዳር 19 ቀን 2015 የሌማት ትሩፋት መርሓ-ግብር ሕብረተሰቡ የተመጣጠነና ጤናማ ይዘት ያለው ምግብ እንዲያገኝና የጥምር ግብርናን የሚያበረታታ መሆኑን የኦሮሚያ ግብርና ቢሮ ገለጸ።

በጅማ ዞን ደረጃ “የሌማት ትሩፋት” ማስተዋወቂያ መርሃ-ግብር በጅማ ከተማ ፊሾ ግብርና ምርምር ማዕከል ተካሄዷል።

በመርሃ-ግብሩ ላይ የተገኙት የክልሉ የግብርና ቢሮ ምክትል ሀላፊ ዶክተር አሚና አብዱረህማን እንዳሉት የሌማት ትሩፋት ህብረተሰቡ የተመጣጠነና ጤናማ ይዘት ያለው ምግብ እንዲያገኝና ጥምር ግብርናን የሚያበረታታ መሆኑን ተናግረዋል።

መርሓ ግብሩ የተመጣጠነ ምግብ በበቂና እና በጥራት በማምረት እንዲሁም በተመጣጣኝ ዋጋ ለዜጎች በማድረስ ሂደት የተሻለ ዕድል ይፈጥራልም ብለዋል።

በተለይም በክልሉ የወተት፣ የማር፣ ፍራፍሬ፣ የእንቁላልና ቀይ ስጋ በስፋት እንዲቀርብ በማስቻልም ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለውም ገልጸዋል።

ይህም ለክልሉ ሕዝብ ተጨማሪ ገቢና የስራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ የህብረተሰቡን የአመጋገብ ስርዓት ያሻሽላል ብለዋል።  

የጅማ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ቲጃኒ ናስር በበኩላቸው የሌማት ትሩፋት መርሓ ግብርን በዞኑ ለመተግበር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

የጅማ ዞን የተለያዩ የግብርና ስራዎችን በስፋት እያከናወነ መሆኑን ገልጸው ቀደም ብለው የተጀመሩ የሌማት ትሩፋትን የሚያጠናክሩ ስራዎች በስፋት ይከናወናሉ ብለዋል።

''ዞኑ ለማር ምርት፣ ለከብት ማድለብ እና እርባታ እንዲሁም ለዶሮ እርባታ አመቺ በመሆኑ የሌማት ትሩፉት ፕሮጀክትን በተሻለ ሁኔታ እንተገብረዋለን'' ሲሉም ተናግረዋል።

የጅማ ዞን የግብርና ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ መሀመድጣሀ አባፊጣ በበኩላቸው መርሓ ግብሩን ለማጠናከር በግብርና ዘርፍ ማሕበር የተደራጁ ወጣቶች በዶሮ እርባታ ላይ አተኩረው እንዲሰሩ ይደረጋል ብለዋል።

በዚህም 2 ሚሊዮን የዶሮ ጫጩቶች ለማህበራቱ ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው የሌማት ትሩፋትን የሚያጠናክሩ ሌሎች የግብርና ስራዎችም ይከናወናሉ ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም