የበይነ መረብ አስተዳደር ጉባኤ ለአፍሪካ የኢንተርኔት ችግሮች መፍትሄ የሚያመላክት መሆን አለበት---የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር

254

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 19 ቀን 2015 በኢትዮጵያ የሚካሄደው የበይነ መረብ አስተዳደር ጉባኤ ለአፍሪካ የኢንተርኔት ችግሮች መፍትሄ የሚያመላክት መሆን እንዳለበት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ ተናገሩ።

17 ኛው ዓለም አቀፍ የበይነ መረብ አስተዳደር ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

ከጉባኤው ጎን ለጎን የዓለም አቀፉ የበይነ መረብ አስተዳደር ጉባኤ ከፍተኛ የመሪዎች መድረክ ተካሂዷል።

ለ2 ዓመት የጉባኤው የከፍተኛ መሪዎች አባሏና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ የበይነ መረብ አስተዳደር ጉባኤ ኢንተርኔትን ለዜጎቻቸው ማዳረስ ላልቻሉ ሀገራት መፍትሄ የሚሆኑ ጉዳዮች የሚኑሱበት እንዲሆን ጠይቀዋል።

በጉባኤው በከፍተኛ መሪዎች የሚነሱ ሃሳቦች ያደጉ ሀገራት ላይ ያተኮሩ ብቻ መሆን የለባቸውም ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ አፍሪካውያን ገና ለዜጎቻቸው ኢንተርኔትን ለማዳረስ ሩጫ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የአፍሪካ ሀገራት የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ ጀማሪ እንደመሆናቸው መጠን ኢንተርኔትን ለዜጎች እኩል ማዳረስ ላይ እገዛ እንዲያደርጉም መጠየቃቸውን ከሚኒስቴሩ ማህበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

17ኛው ዓለም አቀፍ የበይነ መረብ አስተዳደር ጉባኤ ዛሬ የተጀመረ ሲሆን ነገ ዋናው መክፈቻ ይከናወናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም