ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ኢስዋቲኒ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ዙርያ ላሳየችው ጠንካራና ሚዛናዊ አቋም ምስጋና አቀረቡ

157

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 19/2015 ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ኢስዋቲኒ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ዙርያ ላሳየችው መርህን መሰረት ያደረገ ጠንካራና ሚዛናዊ አቋም አድናቆታቸውን ገለጹ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከኢስዋቲኒ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቱሊሲል ድላድላ ጋር ተወያይተዋል።

በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ እና በፕሪቶሪያ ስለተፈረመው የሰላም ስምምነት ላይ አቶ ደመቀ ገለጻ አድርገዋል።

የሰላም ስምምነቱ ተግባራዊ እንዲሆን የኢትዮጵያ መንግሥት ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸው ሀገሪቱ ለዘላቂ ሰላም ተስፋ ሰጪ ሁኔታ ላይ ትገኛለች ብለዋል።

አቶ ደመቀ አክለውም ኢትዮጵያ ፈተና በገጠማት ወቅት ኢስዋቲኒ ላሳየችው መርህን መሰረት ያደረገ፣ ጠንካራና ሚዛናዊ አቋም አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡

የኢስዋቲኒ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በበኩላቸው በተደረሰው የሰላም ስምምነት የኢስዋቲኒ መንግስት የተሰማውን ደስታ ገልጸው ለስምምነቱ ስኬታማ ተግባራዊነት አገራቸው ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን አረጋግጠዋል።

የኢስዋቲኒ መንግሥት ከኢትዮጵያ ጋር ላላት ግንኙነት ልዩ ቦታ እንደምትሰጠው የገለጹት ሚኒስትሯ ለጋራ ጥቅም ግንኙነቱ ወደ አዲስ ከፍታ ማሸጋገር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ሚኒስትሮቹ በኢትዮጵያ እና በኢስዋቲኒ መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ወዳጅነት እና ስትራቴጂካዊ የባለብዙ ወገን ትብብር ለማጠናከር በጋራ ለመስራት መግባባት ላይ መድረሳቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያሳያል።

በቀድሞ ስሟ ስዋዚላንድ በመባል የምትታወቀው ኢስዋቲኒ በደቡባዊ የአፍሪካ ክፍል የምትገኝ ሲሆን በዓለማችን በንጉሳዊ አስተዳደር ከሚተዳደሩ ጥቂት አገራት መካከል አንዷ መሆኗን መረጃዎች ያሳያሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም