በዓለም ዋንጫው ጋና እና ካሜሮን የምድብ ሁለተኛ ጨዋታቸውን ዛሬ ያደርጋሉ

212

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 19 ቀን 2015 በኳታር አስተናጋጅነት እየተካሄደ የሚገኘው 22ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ጋና እና ካሜሮን የምድብ ሁለተኛ ጨዋታቸውን ዛሬ ያደርጋሉ።

የፊፋ ዓለም ዋንጫ ከተጀመረ ዛሬ ዘጠነኛ ቀኑን አስቆጥሯል።

በምድብ ሰባት በአል ጃኑብ ስታዲየም በመጀመሪያ ጨዋታቸው ሽንፈት ያስተናገዱት ካሜሮንና ሰርቢያ ከቀኑ 7 ሰአት ላይ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል።

የማይበገሩት አንበሶች በሚል ቅጽል ስም የሚታወቁት ካሜሮኖች በስዊዘርላንድ 1 ለ 0 እንዲሁም ሰርቢያ በብራዚል 2 ለ 0 መሸነፋቸው የሚታወስ ነው።

በምድብ ስምንት ጋና በኢጁኬሽን ሲቲ ስታዲየም ከቀኑ 10 ሰአት ከደቡብ ኮሪያ ጋር ጨዋታዋን ታደርጋለች።

ጥቋቁሮቹ ከዋክብቶች በመጀመሪያ የምድብ ጨዋታቸው በፖርቹጋል 3 ለ 2 የተሸነፉ ሲሆን ኮሪያ ሪፐብሊክ ከኡራጓይ ጋር ያለ ምንም ግብ አቻ ተለያይታለች።

በምድብ ሰባት ከምሽቱ 1 ሰአት የአምስት ጊዜ የዓለም ዋንጫ አሸናፊዋ ብራዚል በስታዲየም 974 ከስዊዘርላንድ ጋር ትጫወታለች።

በምድብ ስምንት በሉሳይል ስታዲየም ፖርቹጋል ከኡራጓይ ከምሽቱ 4 ሰአት ጨዋታቸውን የሚያደርጉ ይሆናል።

ትናንት በተደረጉ ጨዋታዎች የሞት ምድብ የሚል ስያሜ ባገኘው ምድብ አምስት ሲጠበቅ የነበረው የጀርመንና ስፔን ጨዋታ አንድ አቻ በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

በዚሁ ምድብ ኮስታሪካ ጃፓንን 1 ለ 0 ረታለች።

በምድብ ስድስት ሞሮኮ ቤልጂየምን 2 ለ 0 በማሸነፍ ያልጠተበቀ ውጤት ስታስመዘግብ ክሮሺያ ካናዳን 4 ለ 1 ማሸነፍ ችላለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም