በተቀናጀ የዘር ብዜት ዘዴ ምርታማነታችንን ማሳደግ ችለናል--በኦሮሚያ ክልል ጊምቢቹ ወረዳ አርሶ አደሮች

157

አዲስ አበባ(ኢዜአ) ህዳር 18/2015 በተቀናጀ የዘር ብዜት ዘዴ በመታገዝ ምርታማነታቸውን ማሳደግ እንደቻሉ በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ጊምቢቹ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለጹ።

የተቀናጀ የዘር ልማት ፕሮጀክት አርሶ አደሩን በተለያዩ ምርቶች ምርታማነቱን ለማሳደግ እንዲያስችል የተቀረጸ ፕሮጀክት ነው።

ፕሮጀክቱ እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር ከ2016  ጀምሮ በኢትዮጵያ መንግስት እና "ባዬቨርስቲ ኢንተርናሽናልና ሲያት" በተሰኘ ተቋም ትብብር ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል፡፡

ፕሮጀክቱ የተሻሻሉ ዝርያዎችን ለአርሶ አደሮች ተደራሽ የሚሆኑበት ሲሆን፤ የፓስታና ሞኮሮኒ ስንዴ፣ሽንብራ፣ባቄላ፣ማሽላና ዳጉሳ ምርቶች ላይ በኦሮሚያ፣አማራና ትግራይ ክልሎች ተግባራዊ ሲደረግ  ቆይቷል።

በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ግንቢቹ ወረዳ በፕሮጀክቱ ታቅፈው የፓስታና ሞኮሮኒ ስንዴ ላይ ውጤታማ የሆኑ አርሶ አደሮች የስንዴ ማሳ በተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተጎብኝቷል።    

      

የጉብኝቱ ዓላማም የፕሮጀክቱ አተገባበር ምን ይመስላል?፣አርሶ አደሮች ምን ውጤት አገኙ በቀጣይም ምን ዓይነት ድጋፎችን ይፈልጋሉ? የሚለውን ለመቃኘት መሆኑ ተገልጿል።

አርሶ አደር አቤቤ ወንድሙ በፕሮጀክቱ አማካኝነት የፓስታና ሞኮሮኒ ስንዴ በጥሩ ሁኔታ እያመረቱ መሆኑን ለኢዜአ ተናግረዋል።      

አሁን ላይ በሄክታር እስከ 80 ኩንታል ምርት እየጠበኩ ነው ያሉት አርሶ አደር አቤቤ፤ ይህም በፕሮጀክቱ ከመታቀፌ በፊት ከነበረው ምርታማነት የተሻለ ነው ብለዋል።    

ምርት ካመረትን በኋላ ወደ ገበያ ለማውጣት በሚደረገው ጥረት የደላላ ጣልቃ ገብነት ትልቅ ፈተና ሆኖብናል ሲሉ የገለጹት አቶ አቤቤ፤ መንግስት ጉዳዩ ላይ ሊሰራ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል፡፡   

አርሶ አደር ዘርፌ ጌታቸው በበኩላቸው በፕሮጀክቱ አማካኝነት 10 ኩንታል የተሻሻለ የስንዴ ዘር በማሳቸው በማባዛት በውጤታማነት የስንዴ ልማት እያከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በማሳቸው ያባዙትን የተሻሻለ የስንዴ ዘር በቀጣይ ለሌሎች ሴት አርሶ አደሮች ተደራሽ እንደሚያደርጉም ተናግረዋል፡፡   

በባዬቨርስቲ ኢንተርናሽናል ሲያት ተቋም የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ዶክተር ደጀኔ ካሳሁን በበኩላቸው በጊንቢቹ ወረዳ 550 ሄክታር መሬት በፓስታና ሞኮሮኒ ስንዴ ምርት መሸፈኑን ተናግረዋል።

አርሶ አደሩ ውጤታማ መሆኑን በተደረገ ጥናት አይተናል ያሉት አስተባባሪው ለዚህም በፕሮጀክቱ አማካኝነት የተደረገው ክትትልና ድጋፍ ወሳኝ ሚና ተጫውቷል ብለዋል።

አርሶ አደሩ የገበያ ችግር እንዳይገጥመው ከምግብ አቀነባባሪ ፋብሪካዎች ጋር በቀጥታ የሚገናኙበት ሁኔታዎች የማመቻቸት ስራ እየተሰራ መሆኑንም አክለዋል።  

በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን አድአ ወረዳ ላይ በበሽታ ምክንያት ሽንብራ ምርት ቆሞ ነበር ያሉት ዶክተር ደጀኔ ፕሮጀክቱ ተግባራዊ ከሆነ ወዲህ ግን ምርቱ መቀጠሉን ተናግረዋል።

ዳጉሳ በሚመረትባቸው አካባቢችም በሄክታር እስከ 28 ኩንታል ምርት እየተገኘ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም ሌላኛው የፕሮጀክቱ ስኬት መሆኑን ጠቅሰዋል።     

በፕሮጀክቱ 203 ሺህ አርሶ አደሮችን ተደራሽ ለማድረግ እቅድ መያዙንና እስካሁን ወደ 180 ሺህ አርሶ አደር ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉንም ተናግረዋል፡፡  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም