በ30 ቢሊዮን ብር ወጪ 3 የአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ተገንብተው ለባለሃብቶች ክፍት ሆኑ

100

ባህር ዳር፣ ህዳር 17 ቀን 2015 (ኢዜአ) መንግስት የኢንዱስትሪ ዘርፉን ለማሳደግ በ30 ቢሊየን ብር ወጪ ያስገነባቸው ሶስት የአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ግንባታ አጠናቆ ለባለሃብቶች ክፍት ማድረጉን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገለጸ።

የቡሬ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለባለሃብቶች ለማስተዋወቅ በተዘጋጀው የኢንቨስትመንት ፎረም 103 ባለሃብቶች ገብተው ለማልማት ውሳኔያቸውን አሳውቀዋል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ በኢንቨስትመንት ፎረሙ ላይ እንደተናገሩት፤ በክልሉ የግብርናው ምርትና ምርታማነት ማደግ የኢንዱስትሪው ዘርፍ እንዲፋጠን ምቹ ሁኔታ እየፈጠረ ነው።

ይሄን በመገንዘብም በግብርናው ምርት ላይ እሴት በመጨመር ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የሚያስችል የቡሬ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ መገንባቱን ተናግረዋል።

በፓርኩ የአስፓልት መንገድ፣ የውሃ፣ የኤሌክትሪክ፣ የአንድ ማዕከል፣ደረጃው የጠበቀ የቆሻሻ ማስወገጃ፣  የኢንተርኔትና ሌሎች መሰረተ ልማቶች የተሟሉለት መሆኑን አስገንዝበዋል።

ይሄን በመገንዘብም አቅም ያላቸው ባለሃብቶች ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኩ በመግባት ባጭር ጊዜ ወደ ምርት በመሸጋገር ራሳቸውን ጠቅመው በአገሪቱ ብልጽግና ላይ አሻራቸውን እንዲያሳርፉ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል በበኩላቸው መንግስት በሙሉ አቅሙ ድህነትን ለማጥፋት በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በዚህም የፌደራል መንግስት በአገሪቱ በሚገኙ ሰባት ኮሪደሮች ላይ የአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪዎችን ለመገንባት አቅዶ አራቱን ማስጀመሩን ገልፀዋል።

ከእነዚህ ውስጥም በ30 ቢሊየን ብር ወጭ ያስገነባቸውን የቡሬ፣ ቡልቡላና ይርጋለም የአግሮ ፕሮሰሲንግ ፓርኮች በማጠናቀቅ ለአልሚ ባለሃብቶች ክፍት ማድረጉን ገልጸዋል።

ከዚህ ውስጥም በአማራ ክልል ስምንት ቢሊየን ብር ወጭ የተደረገባቸው ሰባት የሽግግር ማዕከላትና የቡሬ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ እንደሚገኙበት ተናግረዋል።

የኢንዱስትሪ ፓርኮቹ የስራ እድል ለመፍጠር፣ ለቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የውጭ ምንዛሬ ለማስገኘትና ተወዳዳሪ ባለሃብት ለመፍጠር ምቹ ሁኔታ የሚፈጥሩ መሆናቸውን ገልፀዋል።

"በአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ገብቶ ማልማት ዘርፈ ብዙ ጥቅም አለው" ያሉት ደግሞ የሪች ላንድ ፋብሪካ ባለቤት አቶ ሙላት መንገሻ፤ ባለሃብቱ ለኢንቨስትመንት ወጪ ሲያወጣ መንግስትም በዚያው ልክ ወጪ በማውጣት ድጋፍ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።

በፓርኩ ወስጥ ማልማት የ9 ዓመት የታክስ እፎይታን፣ የኮንስትራክሽንና የፋብሪካ ማሽነሪዎችን ከቀረጥ ነጻ በማስገባት አገሪቱ መቶ በመቶ ድጎማ በማድረግ ለባለሃብቱ የበለጠ ጠቀሜታ የሚያስገኝ ነው ብለዋል።

በባህር ዳር በተካሄደው የኢንቨስትመንት ፎረም 103 ባለሃብቶች በቡሬ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ገብተው ለማልማት ውሳኔያቸውን አሳውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም