የአማራ አቀፍ ልማት ማህበር ከግማሽ ቢሊዮን ብር ወጪ የልማት ሥራዎች እያከናወነ መሆኑን አስታወቀ

85
ባህር ዳር መስከረም 17/2011 የአማራ አቀፍ ልማት ማህበር /አልማ/ ከግማሽ ቢሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የክልሉን ህዝብ ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ሥራዎች እያከናወነ መሆኑን አስታወቀ። ማህበሩ አዲስ አበባ ከሚኖሩ የክልሉ ተወላጆችና የልማቱ ደጋፊዎች በአምስት ሚሊዮን ብር የገዟቸውን 10 አምቡላንሶችም ዛሬ ለክልሉ ጤና ቢሮ አስረክቧል። አምቡላንሶቹ በተለይ በገጠር የሚገኙ የነፍሰጡር እናቶችን ወደጤና ተቋም ፈጥኖ በማድረስ በክልሉ የሚስተዋለውን የእናቶችና ህፃናት ሞትን በመቀነስ ችግሩን እንደሚያቃልሉ ተገልጿል። የአልማ ዋና ሠራ አስፈፃሚ ወይዘሮ ብስራት ጋሻውጠና በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት ማህበሩ ከአባላትና ከረጅ ድርጅቶች በሚያሰባስበው ገንዘብ የክልሉን ህዝብ ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ስራዎች እያከናወነ ነው። በያዝነው በጀትም ማህበሩ ከግማሽ ቢሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የትምህርት፣ የጤናና በወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ትኩረቱን አድርጎ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል። በተለይ በትምህርት ጥራት የሚስተዋለውን ችግር ለማቃለል ማህበሩ ለቅድመ መደበኛ ትምህርት የተለየ ትኩረት ሰጥቶ ከትምህርት ቢሮው ጋር ተባብሮ እየሰራ ይገኛል ብለዋል። በጭቃ የተሰሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ወደ ብሎኬት የመቀየርና ደረጃቸውን የማሳደግ፣ አዳዲስ የሁለተኛ ደረጃ፣ የመሰናዶና የቴክኒክና ሙያ ተቋማትን መገንባትና የማስፋፋት ሥራ እያከናወነ ወይዘሮ ብሥራት ጠቁመዋል። ለሥራ አጥ ወጣቶች የተለያዩ ስልጠናዎች በመስጠት ሥራ እንዲፈጥሩ ድጋፍ እያደረገ ይገኛልም ብለዋል። በጤናው ዘርፍም ለጤና ተቋማት የማስፋፊያ ግንባታዎችንና የውስጥ ቁሳቁስ የማሟላት፣ እንዲሁም የስነ-ተዋልዶ ጤና ግንዛቤ ስራዎች እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል። በተጨማሪም በክልሉ ለሚገኙ 110 የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ኦፍ ላይን ዲጅታል ላይብረሪ በቅርቡ ለማስገባት ዝግጅት እያደረገ መሆኑንም ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ  ገልጸዋል። የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አበባው ገበየሁ አምቡላንሶቹን ሲረከቡ እንደተናገሩት አልማ በክልሉ በትምህርትና በጤና በሚያከናውናቸውቸው ስራዎች የተሻለ ውጤት እያስመዘገበ ይገኛል። በአባላቱና በልማት አጋሮቹ ተገዝተው ዛሬ የተረከብናቸውን አምቡላንሶችም የእናቶችና ህፃናት ሞትን ለመቀነስ እየሰራን ላለነው ስራ የተሻለ ውጤት ለማምጣት ያግዛሉ ብለዋል። አምቡላንሶቹንም ችግር ላለባቸው ወረዳዎች በመስጠት በትራንስፖርት የሚቸገሩ ነፍሰጡር እናቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሰራም ተናግረዋል። የኦሮሞ ብሄረሰብ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ ሲስተር ፋጡማ ሰኢድ በበኩላቸው ከአልማ የተሰጣቸው አምቡላንስ የእናቶችና ህፃናት ሞትን ለመታደግ የሚኖረው ድርሻ የጎላ ነው ብለዋል። የደቡብ ወሎን ዞን ጤና መምሪያን ወክለው የአምቡላንሱን ቁልፍ የተረከቡት አቶ መለሰ በላይ በበኩላቸው አልማ የሚስተዋሉ የልማት ክፍተቶችን በመለየት እየደገፈ እንደሚገኝ ተናገረዋል። የተረከብነውን አምቡላንስም እጥረት ላለበት ወረዳ ለይተን በመስጠት የህዝቡን አንገብጋቢ ችግር ለመፍታት የሚውል ሲሆን፣ አምቡላንሱ ለታለመለት አላማ ብቻ እንዲውልም ተገቢውን ቁጥጥር እንደሚያደርጉ ገልጸዋል። ማህበሩ በአዲስ አበባ የሚገኙ የክልሉ ተወላጆች፣ የአልማ አባላትና የልማት ደጋፊዎች ባዋጡት አምስት ሚሊዮን ብር የገዟቸውን 10 አምቡላንሶች ባለፈው ሳምንት ተረክቧል። አልማ ከአራት ሚሊዮን 700 ሺህ በላይ አባላት በማፍራትም በየዓመቱ ከአባላት መዋጮ እስከ 378 ሚሊዮን ብር በመሰብሰብ ለልማት እያዋለ እንደሚገኝም ታውቋል።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም