የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለግብርና ሜካናይዜሽን የሚያገለግሉ መሳሪያዎችን ለደንበኞቹ አስረከበ

411

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 17 ቀን 2015 የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከጀርመን ልማት ባንክ ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ ለሊዝ ፋይናንስ ደንበኞቹ ያቀረባቸውን የሰብል ማጨጃና መውቂያ መሳሪያዎች አስረከበ።

በርክክቡ ወቅት የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ምክትል ፕሬዝዳንት አስፋው አበራ እና በአዲስ አበባ የጀርመን ልማት ባንክ ዳይሬክተር ዲያና ሄድሪክ ተገኝተዋል።

የባንኩ ምክትል ፕሬዝዳንት አስፋው አበራ፤ ጀርመን የኢትዮጵያ ግንባር ቀደም የልማት አጋር መሆኗን ገልጸው፤ ለግብርና ሥራ ለሚያገለግሉ መሳሪያዎች ግዥ የሚውል ድጋፍ በማድረጓ አመስግነዋል።

ለባንኩ የሊዝ ፋይናንስ ደንበኞች የተላለፊት እያንዳንዱ መሳሪያ በቀን እስከ 1 ሺህ 200 ኩንታል ምርት የመውቃት አቅም ያላቸው መሆኑንም አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ፣ የጀርመን ልማት ባንክ እንዲሁም የግብርና ሚኒስቴር የትብብር ማዕቀፍ በማዘጋጀት ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸው፤ ለዚህም በሊዝ ፋይናንሲንግ የአሰራር ሥርዓት በተለያዩ አካባቢዎች ለሚገኙ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ እየሆኑ ይገኛሉ ብለዋል።

በግብርና ሜካናይዜሽን ፕሮጀክት ከጀርመን ልማት ባንክ በተለቀቀ 13 ሚሊየን ዩሮ 33 ኮምባይነሮች ዘጠኝ ትራክተሮች ለደንበኞች መተላለፋቸውን ገልጸዋል።

በዛሬው እለት ርክክብ የተደረገባቸው አምስት መሳሪያዎችም የዚሁ ፕሮጀክት አካል መሆናቸውን ገልጸው፤ በግዥ፣ በምርት እና በመጓጓዝ ላይ የሚገኙ መኖራቸውንም  ጠቁመዋል።

በአዲስ አበባ የጀርመን ልማት ባንክ ዳይሬክተር ዲያና ሄድሪክ፤ የግብርና መሳሪያዎቹ የግብርና ሥራን በማዘመንና ፈጣን አገልግሎት በመስጠት ረገድ ትልቅ ሚና አላቸው ብለዋል።

ኢትዮጵያ የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን የያዘችውን ስትራቴጂ በመደገፍ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል ነው ያሉት።

የጀርመን ልማት ባንከ በኢትዮጵያ በዘርፉ ለሚከናወኑ የልማት ሥራዎች አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም